ሰው ከምትወቅስ እንደጀግናው ቆርጠህ ተነስ፡፡

264
ሕዳር 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ሁሉም ናት፣ ተወልደው የሚያድጉባት፣ በሜዳዎቿ የሚቦርቁባት፣ በወንዞቿ የሚዋኙባት፣ በተራራዎቿ የሚደሰቱባት፣ እልል ተብሎ የሚዳሩባት፣ ወልደው የሚስሙባት፣ ዘርተው፣ አሽተው የሚቅሙባት፣ ወግ ማዕረግ የሚያዩባት፣ ሀገር ሕይወት ናት፣ ሀገር እናት ናት፣ ሀገር ደስታ ናት፣ ሀገር ከምንም ከማንም በላይ ናት። ሀገር ከሌለ አጊጦ መኖር፣ ሞቶ በክብር መቀበር የለም።
ኢትዮጵያ ጥበብ ናት፤ ኢትዮጵያውያን የሚያጌጡባት፣ ኢትዮጵያ ረቂቅ ቤት ናት ልጆቿ መሠረቷን በአለት ላይ ያደረጓት፣ በጋራ የቀለሷት፣ በጋራ የሚኖሩባት፣ ደም ያፈሰሱላት፣ አጥንት የከሰከሱላት፣ ሕይወት የገበሩላት፣ ኢትዮጵያ ብርሃን ናት ጥቁሮች በአሻገር አይተው የጨለማውን ዘመን የተሻገሩባት፣ የሚሻገሩባት፣ ኢትዮጵያ በሰው እጅ ያልተሠራች፣ በወርቅና በአልማዝ የተለበጠች፣ መሶበ ወርቅ ናት፣ በውስጧ ሕብስት ያለባት፣ ኢትዮጵያ ረቂቅ ናት ተመርምሮ ያልተደረሰባት፣ ኢትዮጵያ ምስጢር ናት ውስጧን ጥበብ የሞላት።
በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ ጠላቶች ስለ ኢትዮጵያ በተነሱ ጀግኖች ሁሉ ተመትተው አልፈዋል። ለመድፈር አስበው በአጭር ቀርተዋል። ጀግና የምትወልድበት ማሕፀኗ አያረጅምና በየዘመናቱ የምትወልዳቸው ጀግኖች፣ በየዘመናቱ የሚነሱትን ጠላቶች እየመቱ አስቀርተውታል። ድንበር የሚጥስ፣ ቀዬ የሚያረክስ ሁሉ በጀግኖች ተመትቶ፣ እንዳልሆን ሆኖ ቀርቷል።
ዛሬም እምዬን ለመድፈር፣ ኢትዮጵያውያንን ለማሳፈር ጠላት ተነስቷል። ታዲያ በእምዬ ኢትዮጵያ ላይ የተነሳውን ጠላት ጀግኖች እየቀጡት፣ እየደመሰሱት ነው። ኢትዮጵያ ልጆቿን ስትጣራ “አቤት ወዴት” ብለው ይሰባሰባሉ። ጭንቀቷን ይሰማሉ። በደሏን ያዳምጣሉ። ትእዛዟን ይቀበላሉ። ባዘዘቻቸው ልክ ሳያጓድሉ ይፈፅማሉ። እምዬ ሆይ ያልሽውን አድርገናል ብለው የምስራች ይናገራሉ። በቤቷ ይከብራሉ። ክብርና ሞገስን ይቸራሉ። ዛሬም እምዬ ተጣርታለች። ልጆቿም “አቤት ወዴት” እያሉ ነው።
እምዬ ጠርታው ከተነሳ፣ ዳሬን አስከብር፣ ጠላቴን ስበር ብላው ጥሪዋን ሰምቶ፣ ትእዛዟን አዳምጦ ግዳጅ ላይ ከሚገኝ አንድ ጀግና ጋር ተገናኝቻለሁ። ነገሥታት ክፍሌ ይባላል። በፊዚክስ ትምህርት ድግሪ አለው። በኮምፒውተር ሳይንስ ተጨማሪ ድግሪ አለው። በፊዚክስ መምሕርነት ለዓመታት አስተምሯል።
ትውልዱ “ለእናት ሀገር ሲሉት ለነብሱ የማይሳሳ፣
ቧልት አያውቅም እንጅ ቁም ነገር አይረሳ፣
የጀግኖቹ፣ የእነውቃው ሀገር አርባያ በለሳ” በተባለለት ቦታ ነው። በለሳ ሲወለዱ ጀግንነት፣ ፅናት፣ አልሞ መምታት፣ ለሀገር መሰጠት፣ አሸናፊነት፣ አይደፈሬነትን ይማራሉ። በለሳዎች ለሀገር ካልዘመትን ብለው አዝማቹን የሚከሱ ጀግኖች ናቸው። መምሕር ነገሥታትም ከዚሁ ሀገር የጀግኖችን ባሕሪ ወርሷል። በበለሳ ቆላማ ቦታዎች እየተመላለሱ ጀግንነት የሚሰሩ፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚያድሉ ጀግኖችን ሲያይ ነውና ያደገው ከጀግንነት በቀር ሌላም አይታዬው።
ከትውልድ ቀዬው ከወጣ በኋላም በነገሥታቱ ከተማ፣ በጀግኖች መገኛ በጎንደር ከተማ ኖሯል። ነገሥታት በመምሕርነት እያገለገለ፣ ዓመታትን አሳልፏል። ታዲያ የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ኀይል በየጊዜው የሚያደርሰው ግፍና በደል ልቡን ያደማዋል። እረፍት ይነሳዋል። እርሱም በሚችለው ሁሉ ይታገለው ጀመር። “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ እኩይ ኀይል ካለ ማን ተደስቶ ይኖራል? የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ኀይል በግፉ ሲቀጥልበት መምሕር ነገሥታትም ከተለመደው ትግሉ ወጣ ብሎ መታገል እንዳለበት አመነ። አደረገውም።
የመምሕርነት ሕይወቱን ጥሎ አሸባሪውና ወራሪውን ኀይል ፊት ለፊት በነፍጥ ለመግጠም ተምዘግዛጊ ነብሩን የአማራ ልዩ ኀይልን ተቀላቀለ። ከእኔ ጋርም የተገናኘነው የቀድሞው መምሕር የአሁኑ ወታደር ጠላትን እየተፋለመ ባለበት ወቅት ነው። ስለ ትግሉ አውግቶኛል። “ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ ተመርቄያለሁ። በኮምፒውተር ሳይንስም ተጨማሪ ድግሪ አለኝ። ለስድስት ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች በመምሕርነት አገልግያለሁ። ከመምሕርነት ባለፈ የትጥቅ ትግል አድርጌያለሁ፤ አሁን ደግሞ ከመምሕርነት ወጥቼ የአማራ ልዩ ኀይልን ተቀላቅዬ እያታገልኩ ነው” ብሏል።
መምሕር ነገሥታት የአማራ ልዩ ኀይልን ተቀላቅሎ አሸባሪውና ወራሪውን ኀይል እየደመሰሰ በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ነግሮኛል። “ወቅቱ የሚጠይቀው ነገር አለ፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን ነገር መሆን ደግሞ የእኔ ፍላጎቴ ነው፤ ሰላም በነበረበት ጊዜ በመምሕርነት ሳገለግል ነበር፤ ሰላም ባልሆነበት ጊዜ ወታደር ሆኜ እያገለገልኩ ነው፤ የዘወትር ጥያቄዬ ሕልውናችን ለምን ይነካል? ነው፤ ሕልውናችንን ለማስከበር እኛ ወጣቶቹ ከፍተኛውን ሚና መጫዎት አለብን፤ ይሄ ዘመን የእኛ ዘመን ነው፤ ይህ ወቅት የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ማድረግና ጠላትን እስከመጨረሻው መደምሰስ ነው፤ እኔም ይሄን ላደርግ ወደድኩ ወደዚህም ገባሁ“ ነው ያለው።
በዘመንህ ሥራበት፣ በዘመንህ ተከበርበት፣ በዘመንህ ዘመንህ ሲያልፍ ሁሉ የማያልፍ ታሪክ ፃፍበት። ከተራራ የገዘፈ ገድል አስቀምጥበት። መምሕር ነገሥታትም እያደረገው ያለው ይሄንኑ ነው። በዘመኑ ጠላትን ማጥፋት፣ ሀገርን ማፅናት፣ ወገንን ማኩራት ነው። ተማሪዎች ነገ ተስፋ እንዲኖራቸው፣ ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ከማስተማር በዘለለ ለሀገር ዘብ እንዲሆኑ ሆኖ ማሳዬት ትልቅ ነገር መሆኑንም ገልጿል መምሕር ነገሥታት። ተማሪዎቼን ስለ ሀገር ከምነግራቸው ሆኜ ሳሳያቸው የበለጠ ያምራል። ሆኜ ሳሳያቸው የበለጠ ይቀበሉኛል ብሎኛል።
ነገሥታት በመምሕርነት ሕይወቱ በመልካም አርዓያነት የሚጠቀስ ትጉህ መምህር እንደነበርም ነግሮኛል። ለውትድርና ሕይወቱም የተለዬ ትኩረትና ፍቅር ሰጥቶ ስልጠናውን እንደወሰደ አስታውሷል። በአሁኑ ሙያውም ለድል እንደሚገሰግስ ነው የገለፀው። ውትድርና ለሀገር ሲባል ራስን አሳልፎ የመስጠት የተከበረ ሙያ ነውም ነው ያለው። ሁሉም ወታደር ቢሆን ወይንም ሁሉም የውትድርና ስልጠናዎችን ቢሰለጥን ለሀገር የተሻለ እድል ይዞ እንደሚመጣም ተናግሯል።
ለሀገር ሕይዎትን መስጠት ትልቁ ስጦታ ነው። ሰው መጠጥ ቤት ተደባድቦ ይሞታል ለሀገር ክብር ሲባል መሞት ግን ትልቅ ክብር ነው ብሏል። “ባለ ትዳር ነኝ፤ የአንድ ልጅ አባትም ነኝ፤ የሚገርምህ ልጄ የተወለደው የካቲት 23 ነው። ልጄም ምኒልክ ነገሥታት ይባላል። የካቲት 23 ለእኔ ታሪካዊ ቀን ነው። በጣም የማከብረው፣ የምወደው ቀን ነው። ቀኑን በተለዬ ሁኔታ ነው የማከብረው። በዚያ ትልቅ ቀን ልጄ በመወለዱ በጣም ደስተኛ ነኝ። የልጄና የባለቤቴ ጉዳይ እኔን አልገደበኝም። እኔ ግንባር ገብቼ ካልተፋለምኩ ልጄና ባለቤቴ ሰላም መሆን አይችሉም። እነርሱን ለማዳን መዋጋትና ድል ማድረግ አለብኝ” ነው ያለኝ።
መምሕር ነገሥታት በሚወደው ቀን ለበረከት የተሰጠውን የሚወደውን ልጁን፣ የሚወዳትን ባለቤቱን፣ የሞቀ ቤቱን ጥሎ ከሁሉም በላይ ለሆነችው ሀገር ሲል መዋጋትን መረጠ። ለውትድርና አደላ።
ሌላ አስገራሚ ነገርም ነገረኝ። ውስጤን ቢያሳዝነውም ፅናቱ ግን አስገረመኝ። “አባቴ ትግል ላይ እያለሁ አርፏል፤ አባቴን አፈር ማልበስ አልቻልኩም።
´እናት አባት ሲሞት ባገር ይለቀሳል፣
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል` እንደሚባለው ሀገሬን አስቤ ለሀገሬ አንድ ጠላት እንኳን መምታት ትልቅ ነገር ነው ብዬ ቀርቻለሁ። አባቴ የሞተው ታሞ ነው። ጠላት ምንም በደል ሳይኖርባቸው የሚገድላቸው ወገኖቼ ደም እኔን ይጠራኛል። ሕይወቴ ይሄ ነው። ሀብትና ንብረት ያላቸውን ሰዎች ከሞት የታደጋቸው የለም፤ ቤተሰባዊ ሁኔታዬ የበለጠ እንድጠነክር ያደርገኛል እንጂ ወደ ኋላ አይጎትተኝም“ ነው ያለኝ።
ሀገሩን ከሁሉም አስበልጧል። ከአባቱ ቀብር ላይ ከመቆም ከሀገሩ ድንበር ላይ መቆምን አስቀድሟል። ሰው ወታደር ሲሆን ወደ ሞት እየሄደ አይደለም፣ ብዙ ጀብዱዎችን ሊፈፅም እየሄደ እንደሆነ መታሰብ አለበት ነው ያለው። እኔን አምኜበት ከምጓዝበት መንገድ ማንም እንዲያሰናክለኝ አልፈቅድም፣ አልፈልግምም ነው ያለኝ።
“ከልጅነቴ ጀምሮ ስንቀሳቀስ ትጥቅ መያዝ ደስ ይለኛል፤ እኔ ባደኩበት ማኅበረሰብ አንድ በሬ ካለው ሁለተኛ በሬ መግዛት አይፈልግም፤ ሁለት በሬ ከመግዛት ይልቅ አንድ ክላሽ ገዝቶ በቀንጃ ቢያርስ ይወዳል፣ ያ ለእኔ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል፤ ያልገዛም ባይነት መንፈስ አለ፤ ብዙ ጀግኖችን እያየሁ ነው ያደኩት፤ በግፍ አገዛዝ አልገዛም ብለው የሸፈቱ ጀግኖችን እያየሁ ነው ያደኩት፣ እነርሱ የሸፈቱት ለነፃነት ነው፣ ለእኔ እነርሱ ትልቅ መሠረቶቼ ናቸው፤ እኒያን መሠረቶቼን አሸባሪው ቡድን በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ሽፍታ ናቸው እያለ ብዙ ጀግኖችን ገድሏል፤ ቢያንስ እኔ ዛሬ የእነርሱን ደም እመልሳለሁ” ብሏል መምሕር ነገሥታት በቁጭትና በእልህ። ጀግኖች የሸፈቱት፣ አልገዛም ያሉት ለክብር ነውም ብሎኛል።
“ሻንጣዬን ፈትሽ ከሬንጀር ውጭ ሌላ ልብስ የለኝም፤ ከሞትኩም እስከነ ሬንጀሬ ነው፤ እስከመጨረሻ ጥይቴ ተዋግቼ እሞታለሁ እንጂ እኛ በዘራችን እጅ መስጠት አናውቅም፤ እጅም አልሰጥም፤ ጠላት የእኔን እጅ አይዛትም” ነው ያለው። ወኔው፣ ቁጭቱ፣ ጀግንነቱ ግሩም ነው። እጅ መስጠት፣ ጠላት ሲመጣ ቁጭ ብሎ ማዬት በዘሩ የለም። የእርሱ ዘር ወራሪን መቅጣት፣ ሀገርን ማፅናት ሕዝብን ነፃ ማውጣት ነው የሚያውቁት። እርሱም የእነርሱን ነው የወረሰው። ጉዟችን እስከ ቀራንዬ ነው እንደሚባለው የእኔም ጉዞ አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይል ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ነው ብሎኛል።
ጠላት አማራን ለማጥፋት ያልሄደበት ርቅትና መንገድ አለመኖሩንም ነግሮኛል። ይህ ጊዜ የእኛ ጊዜ ነው። ለዓመታት በደል የደረሰበትን ሕዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ ማድረግ አለብን፣ መዝመት በሚገባን ጊዜ ሁሉ መዝመት አለብን። አንድ ጠላት ይዞ መሞት ትልቅ ጥቅም አለው ብሏል።
‟ሁሌም ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ እሆናለሁ” መምሕር ነገሥታት ከራሱ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ነው። በጀግንነቱ እና በቁርጠኝነቱ ተደምሜ አመስግኜ ተሰናበትኩት።
ታዲያስ አንተስ ለምን ወቅቱ የሚጠይቀውን አትሆንም? ሀገር ስትጠራህ ለምን አቤት አላልክም? ዛሬ ስትጠራህ አቤት ካላልካት ነገ ስታጣት የምትጠለልበት ያጣህ ባተሌ ትሆናለህ። ወቅቱ የሚጠይቀውን ለመሆን ተነስ፣ ወደ ድል ገስግስ፣ እምዬ ጠርታሃለችና አቤት ወዴት በላት። አዎን አንተም እንደርሱ ቆራጥ ሁን። ሰው ከምትወቅስ እንደርሱ ቆርጠህ ተነስ። ምቾትን እርሳ። ለሀገርህ ድረስላት፣ የሚወጋትን እሾህ ንቀልላት።
በታርቆ ክንዴ
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለህልውና ዘመቻው ድጋፍ በአቴንስ፣ በሮምና በቱሪን ከተሞች በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ከ33 ሺህ ዩሮ በላይ መሰብሰቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleሂድ በጀግንነት የወንድምህን እና የሀገርክን ጠላት ደምስስ፡፡