አሜሪካ ከ30 ዓመታት በኋላ በሶማሊያ ኤምባሲዋን ከፈተች፡፡

157

ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2012 ዓ/ም (አብመድ) ሶማሊያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ አሜሪካ ዘግታው የነበረውን የሞቃዲሾ ኤምባሲዋን መልሳ ከፈተች፡፡

ሀገሪቱን ለረዥም ዓመታት የመሩት ዚያድ ባሬ በ1991 (እ.አ.አ) ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ሶማሊያውያን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ገብተው ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ሀገራት ኤምባሲዎቻቸውን ዘግተዋል፤ አሜሪካም አንዷ ነበረች፡፡

በተለይ ሶማሊያ የአክራሪ ሽብርተኞች መናኸሪያ መሆን በመጀመሯ ከብዙ ሀገራት ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋርጦ ነው የቆየው፡፡

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ቋሚ ዲፕሎማቶችን በሞቃዲሾ ያስቀመጠችው አሜሪካ ትናንት እንዳስታወቀችው ደግሞ ኤምባሲዋን እንደገና ከፍታለች፡፡

በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ‹‹የኤምባሲው መልሶ መከፈት ጉልህ ጠቀሜታ ያለውና ታሪካዊ ነው፡፡ በ2013 (እ.አ.አ) የአሜሪካ መንግሥት ለሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት የሰጠውን ዕውቅናም የሚያጠናክር ነው›› ብለዋል፡፡

አሜሪካ የሶማሊያ ትልቋ የዕርዳታ ምንጭ ስትሆን ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ 730 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡ አሸባሪውን አልሸባብ በመዋጋት በኩልም አሜሪካ ትልቅ ድርሻ እንዳላት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ አካባቢ እና ጎንደር ከተማ አዘዞ ክፍለ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በከተማዋ እና በአካባቢው አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።
Next articleበጎንደር ከተማ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተበክሏል እየተባለ በማኅበራዊ ገጾች የተለቀቀው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ተገለፀ።