
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ነች፤ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በፈጸመው ክህደት ጦርነቱ ከተጀመረም አንድ ዓመት ሞልቶታል። ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይዎት ተቀጥፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ የሰብዓዊ ችግር ተዳርገዋል።
አሽባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ሀገር የማፍረስ ቅዠቱን እውን ለማድረግ ተደጋጋሚ የሀገር ክህደት ድርጊቶችን ፈጽሟል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ በሰነዘረው ጥቃት ሊያፍር እና ሊጸጸት ይገባው ነበር፤ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ሰኔ መጨረሻ ላይ ለትግራይ ሕዝብ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደመልካም አጋጣሚ ወስዶ መጠነ ሰፊ ወረራ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጀመረ። በዚህም መጠነ ሰፊ ወረራ፣ አያሌ ውድመት እና ዘረፋ በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተፈጽሟል፤ እየተፈጸመም ይገኛል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ከሌላኛው የሽብር ቡድን ኦነግ ሸኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር ችግሩን ሀገራዊ የህልውና ስጋት ለማድረግ ተሸጋግረዋል።
የሽብር ኀይሎቹ የፈጠሩትን የሕልውና አደጋ አንዳንድ የውጭ ሀገራት ምዕራባውያን እና በተለይም ደግሞ አሜሪካ በህቡዕ እና አልፎ አልፎም በግልጽ ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህም ኢትዮጵያን ላልተቋረጠ የእርስ በእርስ ጦርነት በመዳረግ ከሀገሪቱም አልፎ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማመስ ያለመ መሆኑ እሙን ነው፡፡
በሌሎች ሀገራት ላይ እንደዳረጉት ሁሉ ጣልቃ ገብተው ቀጣናውን ወደለየለት ፍርስራሽነት የመቀየር ዓላማን ያነገበ መሆኑ ቀስ በቀስ መሻታቸው ገሀድ እየወጣ ነው።
ከሰሞኑ በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍ ፌልትማን ወደ አዲስ አበባ መምጣት የሚነግረንም 1983 ዓ.ም በጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም መንግሥት ላይ ያነጣጠረውን የኽርማን ኮህንን ልዩ ተልዕኮ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት ብቻ ከ11 ጊዜ በላይ ተሰብስቦ ረብዓልባ ውሳኔ ላይ መድረሱም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴዋ ኢትዮጵያ ላይ ደባ የሠራውን ሊግ ኦፍ ኔሽንን እንድናስታውስ አስገድዶናል።
ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን መፃዒ እጣ ፋንታ የመወሰን መብትም ሆነ አቅም ያላቸው ራሳቸው ኢትዮጵያውያን እንጂ ሞግዚት የመሆን መሻት ያላቸው የውጭ ኃይሎች አይደሉም። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ለኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ድጋሜ ወደ ሥልጣን ቢመጣ የሚያመጣበትን መከራ ጠንቅቆ ያውቃል። ተስፋ ሳይሆን ስጋት፣ ነፃነት ሳይሆን ባርነት፣ አብሮነት ሳይሆን መለያየት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ቢመጣ ይዟቸው የሚመጣቸው መርገምቶች ስለመሆናቸው ብዥታ የለም።
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግል ጠላት ከሆነ ወራቶች አልፈዋል። ሀገር ለማፍረስ በፈጸመው ወረራ ንጹሃን ሰለባ ሆነዋል፤ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ተፈናቅለዋል፤ ሃብትና ንብረታቸውን በግፍ ተነጥቀዋል፡፡ ቀኛቸውን ያጡ ዜጎች ግራቸውን ደግመው የሚሰጡበት ትዕግስትም ሆነ እንጥፍጣፊ ፍርሃት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የለምና የኢትዮጵያ የመዳን ቀን ስለመቅረቡ አስረጂ አያስፈልግም።
“ባሩድ የማታ ማታ የሚያጠፋው አብዝቶ የተጠቀመውን ነው” ይላሉ አበው ኢትዮጵያውያን። ኢትዮጵያውያን ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ከራሳቸው ሀገር አልፎ የቀጣናው የሰላም ስጋት እንደሆነ ተረድተዋል።
አሜሪካ ታሊባንን እና ቬትናምን አላሸነፈችም። ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽን ደባና ሴራ አልተንበረከከችም። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከየመን እስከ ሊቢያ፤ ከሶሪያ እስከ ኢራቅ ብዙ ተምራለች።
ኢትዮጵያን የሚታደጋት የውጭ ኃይል የሚያንበረክካትም የውጭ ተፅዕኖ ኖሮ አያውቅም፤ ከዚህ በኋላም አያኖርም። እናም የተጀመረው የኢትዮጵያ የትንሳኤ ጉዞ ዳር ሊደርስ ተቃርቧል።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!
በታዘብ አራጋው
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ