ፋኖ ሠንደቁን አስቀድሞ እየገሰገሰ ነው!

1251
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፣ የታሪክ ባላባት፣ የጦር መሪ፣ ድል አድራጊ፣ በግፍ አልገዛም ባይ፣ የነፃነት አባት የጥቁሮች ኩራት፣ ሽንፈት የማያውቀው፣ ፈሪ የሚያስጨንቀው፣ በክንዱ የሚያደቀው፣ ለሀገር ሞት ኩራት፣ ተኮሶ የማይስት፣ ለእናት ሀገሩ ምንም የማይሰስት፣ ይሸሻል ተብሎ የማይጠረጠር፣ በዱር በገደል፣ በምሽግ የማይበገር፣ የባቱ ልጅ። ጥሩ አባት ጀግንነትን ያወርሳል፣ ነፃነትን ያጎናፅፋል፣ ተሸንፎ ማቀርቀር፣ ተገፍቶ መኖር፣ በባርነት መታሰር አይሆንለትም።
በደምና በአጥንት ነፃነት እንደሚወረስ፣ በጀግንነት እና በአሸናፊነት እንደሚገሰገስ፣ ከቀደምቶቹ ተምሯል፤ በዚያ መስመር ይጓዛል። ነፃ ሀገር ተቀብሏል ነፃ ሀገር ያስረክባል። ከአባቱ ጀግንነት፣ አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ፅናት፣ አልሞ ተኳሽነት፣ አይበገሬነት፣ ለነፃነት መሞት፣ በነፃነት መኖር የወረሰው ፋኖ ዛሬም የአባቱን ነፍጥ አንስቶ፣ በእናት ሀገሩ ምሎ ተገዝቶ ለነፃነት እና ለሀገር አንድነት በዱር በገደሉ፣ በሀሩሩ እየተጓዘ፣ ጠላቱን እንደ አገዳ እየቆረጠ ነው።
በደም የተቀበላትን አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ከፊት አስቀድሞ እየገሰገሰ ነው። በደም ቃል ኪዳን የተቀበላት፣ ከነብሱ አስበልጦ የሚወዳት፣ በደምሥሩ ያዋሐዳት፣ ምሎ የሚገዘትባት፣ በመንገዱ ሁሉ ከፊቱ የሚያስቀድማት ሠንደቁ ተነካች ሲባል ፎክሮ ይነሳል። እንደ አንበሳ ያገሳል። እንደ ነብር ተቆጥቶ ነፍጡን አንስቶ፣ ሠንደቁን የደፈራትን፣ ቀዬውን ያረከሳትን፣ ሊቀጣው ይገሰግሳል እንጂ ዝም ማለት አይሆንለትም።
የአባቱ ልጅ ፋኖ ዛሬም ቀዬውን ያረከሰውን፣ ሕዝብ የበደለውን ከሃዲ ኀይል አደብ ሊያስገዛው፣ ይዞ ሊያናዝዘው፣ ቀጥቶ ሊያስተምረው፣ መትቶ ወደ አፈር ሊመልሰው ግስጋሴ ላይ ነው። ሀገር ሊያፈርስ፣ ታሪክ ሊያረክስ የመጣውን የትግራይን ወራሪና አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ፋኖ ቆርጦ ተነስቷል። አፈሙዙ ዞሯል። ጠመንጃው ተውልውሏልና ሳይቀጣ አይመለስም።
ከዳር ዳር እያስተጋባ ወደፊት እየገሰገሰ ነው። እምብኝ ብሎ የተነሳው ፋኖ ጠላቱን ሊደመስስ፣ ታሪኩንም ከፍ አድርጎ ሊያነግስ ነው የዘመተው። የተቆጣው የታጠቀው።
በወሎ ምድር የገባውን ጠላት እየቀጡ ከሚገኙ ፋኖዎች ጋር ተገናኝተናል። ሠንደቃቸውን አስቀድመው፣ የኢትዮጵያን ስም ጠርተው፣ በስሟ ጠላትን ሊያጠፉላት፣ ለክብሯ ሰላምን ሊመልሱላት፣ ጠላትን ከምድሯ ሊነቅሉላት እየደመሰሱላት ነው።
ፋኖ ዘላለም ጥላሁን በወሎ ምድር የገባውን ጠላት እየቀጡት መሆናቸውን ነግረውናል። በገቡባቸው አካባቢዎች ሕዝቡን እያረጋጉ፣ በቀዬው እንዲቆይ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል። ፋኖው ምንም ነገር ቢፈጠር ወደኋላ የማይልና በደል የተፈፀመባቸውን ወገኖች ለመካስ የሚገሰግስ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወራሪውንና አሸባሪውን ኃይል በመደምሰስ ከጠላት ነፃ የሆነ አማራና አንዲት ኢትዮጵያ እንድትፀና የማድረግ ዘመቻ ላይ ስለመሆናቸውም አስታውቀዋል። አማራ ታሪከኛ ነው ያሉት ፋኖው ለጠላቶቻችን ታሪካችንና ጀግንነታችንን ልናሳያቸው መጥተናል ነው ያሉን። ፋኖው ለሕዝቡ መልካም ደስታ ይዞ እንደሚመጣም በእርግጠኝነት መናገር እንደሚችሉ ነው የገለፁት።
የአማራ ሕዝብ በፋኖ ይኮራል፣ ፋኖም የአማራን ሕዝብ ነፃ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል። ወጣቶች በዚህ ሰዓት ምቾትን ረስተው፣ በበደል ውስጥ ላሉ ወገኖች እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ፋኖ ሽታዬ የትዋለ የአማራ ፋኖ ወደ ግንባር ጠላትን ለመደምሰስ መግባቱን ገልፀዋል። ጠላት ፋኖ መጣ ሲባል በስሙ ገና እንደሚበረግግም ነግረውናል። ፋኖ በሚገባበት ሁሉ እየነቀለ እንደሚሮጥም ተናግረዋል። በፋኖ ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማይታወቅም ገልፀዋል።
በአባቶቻችን ታሪክ እስካሁን ቆይተናል ያሉት ፋኖው አሁን ሀገር በእጃችን ላይ ናት፣ ታሪክ የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው፣ ሀገር በእጃችን ስትወድቅ ለማንም ልንሰጣት አይገባም፣ ሁሉም ተነስቶ ጠላትን ከምድረ ገፅ ማጥፋት ይገባዋል፣ ዛሬ ከቤቱ የሚተኛ ካለ ስህተት ውስጥ ነው፣ ጠላቶቻችን በምድር ላይ እንዲቆዩ የሚፈቀድላቸው አይደሉም ነው ያሉት። በአጭር ጊዜ ለሕዝባችን የድል ብሥራት እናቀርባለንም ብለዋል።
ጠላት ከወሬ የዘለለ ተግባር የሌለው ስለሆነ ሀገራችንን ለእርኩስ መጫወቻ ልናደርጋት አይገባም ነው ያሉት ፋኖው።
ሌላኛው ፋኖ ካሳሁን ዘሪሁን ፋኖ ከሁሉም በፊት ሀገር ትቅደም ብሎ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል። የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ቡድን ሕፃናትን ከእናታቸው እቅፍ እየነጠቀ፣ የሚገድል፣ እናቶችን የሚደፍር፣ አማራን ለማጥፋት የተነሳ መሆኑን ያነሱት ፋኖው ሁሉም በአንድ እስትንፋስ የሚተነፍስ ጀግናው ተዋጊ ፋኖ ጠላትን ከገባበት ገብቶ ያጠፋልም ብለዋል።
ፋኖ መነሻውና መዳረሻው ሀገር መሆኗንም አንስተዋል። ፋኖን የቀሰቀሰው ብሶትና የንፁሐን ደም መሆኑንም ተናግረዋል። የጠላትን መነሻ ሥር ነቅለን እንጥለዋለንም ብለዋል። ሀገርን በአጭር ጊዜ ከጠላት ነፃ እናወጣለን ነው ያሉት።
ሌላኛው ፋኖ ወርቅነህ አያሌው ፋኖ በሰላም ጊዜ ሠርቶ የሚበላ፣ ሀገር ተደፈረች ሲባል ደግሞ በራሱ ትጥቅና ስንቅ የሚዘምት፣ ሀገርን ከጠላት ለመከላከል ዝግጁ የሆነ ነው ብለዋል። ዛሬም እንደ ጥንቱ መነሳቱን ነው የተናገሩት። በዚህ ሰዓት ለባርነት የተዘጋጄ ትውልድ ሊኖር አይገባም፣ ነፃ ሀገር ተረክበን በባርነት አንኖርም ብለዋል።
የጎጃም ቀጣና የፋኖ መሪ መቶ አለቃ አሰፋ አድማሱ ጠላት አማራ አንገቱን እንዲደፋ፣ እርስ በእርስ እንዳይግባባ ለማድረግ የተነሳና በደሎችን የፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል። ፋኖ ምንም ነገር ሳይገድበው ጠላት ባለበት ሁሉ የሚዘምትና ጠላትን ለመምታት የተነሳ መሆኑን ገልፀዋል።
ለልጆቻችን ደማቅ ታሪክ ለማቆዬትና የአባቶቻችን ታሪክ ለመድገም እየገሰገስን ነው ብለዋል። ፋኖ ከሌሎች የወገን ኃይሎች ጋር ሆኖ የጋራ ጠላቱን ያጠፋልም ነው ያሉት። ደማቅ ታሪክ እየሠሩ እንደሚጓዝም ተናግረዋል።
ሰላም ከሌለ መኖር ስሌለ ጠላትን ለመፋለም ሁሉም እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል። ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት የተነሳው ጀግናው ፋኖ በአስፈሪ ግርማው፣ በማይስት ማነጣጠሪያው እያለመ ጠላትን እየደመሰሰው ነው። ፋኖ የጥንቱ፣ የሀገር መሠረቱ፣ ድል የአባቱ። ጠላትን የሚቀጣ፣ ድል አድርጎ እየፎከረ የሚመጣ። የጀግኖች ልጅ፣ የጀግኖች ስብስብ።
በታርቆ ክንዴ
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአሸባሪዉን የትግራይ ወራሪ ኀይል ሴራ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዉያን በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸዉን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleየተጀመረው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ጉዞ ዳር ሊደርስ ተቃርቧል።