
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን ትናንት በጎንደር ከተማ ተንቀሳቅሶ ቅኝት አድርጓል። በቅኝቱም በግጭቱ ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ሀብትና ንብረት መውደሙንና ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች መኖራቸውን ተመልክቷል።
ምንም እንኳን መሀል ከተማ ላይ መደበኛ እንቅስቃሴ ቢኖርም በአዘዞ ክፍለ ከተማ የነበረው መደበኛ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ ነው። ከጎንደር ወደ ጭልጋ-መተማ እስከ ሱዳን ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ተቋርጧል።
በሰው እና በንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስና የአካባቢውን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ችግሩ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይል እንዲሁም ወጣቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በትብብር እየሠሩ መሆኑንም ቡድኑ ተመልክቷል።
በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እና የማኅበራዊ ሚዲያ ግጭቱ በቅማንት እና በአማራ ሕዝብ መካከል የተፈጠረ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ተገቢነት የሌለው እና ሕዝቡን ለማደናገር ሆን ተብሎ የተሠራ መሆኑንም የአካባቢው ማኅበረሰብ እየገለጸ ነው። በሕዝቡ መካከል ምንም ዓይነት ግጭት አለመኖሩን በመግለጽ ድርጊቱ መታረም እንዳለበት ኅብረተሰቡ እየገለጸም ይገኛል።
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በየጊዜው በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝብ የሚያደርስ ይሆናል።