“…እኛ እያለን መቼም ስንቅ አይቋረጥም” የእብናት ወረዳ ነዋሪዎች

83
ሕዳር 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ክንደ ነበልባሎቹ የእብናት ወረዳ የቁርጥ ቀን የሀገር ልጆች መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለው “ስንቄን ከራሴ ትጥቄን ከጠላቴ” ብለው ወደ ግንባር ዘምተዋል፡፡ በግንባርም አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ ወደ ፊት እየገሰገሱ መሆኑን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በሥፍራው ተገኝቶ አረጋግጧል።
ሕዝባዊ ሠራዊቱ “ስንቄን ከራሴ” ሲል ይዞት የዘመተውን ስንቅ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ ሕዝባዊ ደጀን የሚያቀርብለትን ጭምር ለመግለጽ ነው፡፡
አሚኮ በእብናት ወረዳና ከተማ አስተዳደር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድ በመሥሪያ ቦታቸው ተገኝተው ለወገን ጦር ስንቅ እያዘጋጁ ነው።
ነጋዴዎች ከንግዱ ማኅበረሰብ ገንዘብ በመሰብሰብ የእርድ ሰንጋ፣ በግ እና ፍየል ገዝተው ወደ ግንባር እየላኩ ነው።
ስንቅ ሲያዘጋጁ ያገኘናቸው ወይዘሮ አበበች ድረስ እንዳሉት “አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ንጹሐንን እየገደለ፣ እህቶቻችንን እየደፈረ፣ ሃብት ንብረት እየዘረፈ እና እያወደመ መቀጠል የለበትም፤ ለዚህም ወንድሞቻችን ወደ ግንባር ዘምተዋል፤ በድል እንደሚመለሱ አንጠራጠርም፤ ለዘማቾች እኛ እያለን መቼም ስንቅ አይቋረጥም” ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኛው በመዝመትና ሌላው ደግሞ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑንም አረጋግጠውልናል።
አቶ እሸቴ መላኩ በእብናት ከተማ ነጋዴ ናቸው፤ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ጠላት አማራ ክልልን ለቆ ሲወጣ እና ሀገር ሰላም ስትሆን መኾኑን ተናግረዋል። ይህንን ታሳቢ ያደረጉት የእብናት ከተማ አስተዳደር የንግዱ ማኅበረሰብ በአንድ ቀን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ 52 ሰንጋ ገዝተው ዋግኽምራ ግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ኀይል ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የእብናት ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ጌታቸው ደጉ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ የመንግሥትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ልኳል። ለሠራዊቱ ሽኝት ከተደረገለት ቀን ጀምሮ የመንግሥት ሠራተኛው ስንቅ እያዘጋጀ ነዉ፤ የንግዱ ማኅበረሰብም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የገዛውን ሰንጋ፣ ፍየል እና በግ በግንባር ተገኝቶ ድጋፍ አድርጓል፤ ድጋፉም የተጀመረው የህልውና ዘመቻ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል የተፈናቀሉ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎችን ተቀብሎ እና እንክብካቤ በማድረግ ወደ ቀያቸው መመለሱንም ጠቅሰዋል፡፡
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል እስኪቀበር ሁለንተናዊ ተሳትፎው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቁት፡፡
ዘጋቢ፦አዳሙ ሽባባው
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ያለ መስዋእትነት ድል አይገኝም!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበኩር ጋዜጣ ሕዳር 06/2014 ዓ.ም ዕትም
Next articleበአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ የወጣ የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት መመሪያ