
ባሕር ዳር: ሕዳር 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ልዩ ኃይል፣ሚሊሻና ሕዝቡ ከሀገር መከለካያ ሠራዊት ጋር በመሆን በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ የሞከረውን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በተባበረ ክንድ እየደመሰሱት መሆኑን የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ገለጹ።
የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ኑር ሳሊን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል እና ሸኔ በአፋር ክልል የኢትዮ- ጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ ወረራ መክፈታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም አሸባሪዎቹ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና በሕዝቡ የተባበረ ክንድ እየተደመሰሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መስመር ጠላት ሚሌን ለመያዝ በማሰብና የጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት ላለፉት 13 ቀናት የማጥቃት ሙከራ ቢያደርግም በተቀናጀ መልሶ ማጥቃት ሳይሳካለት እየተመታ መሆኑን ሰብሳቢው ጠቁመዋል። በዚህም ጠላት ከባድ ኪሳራ እያስተናገደ ይገኛል ያሉት አቶ መሃመድ አሸባሪውን ቡድን የማጥቃት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ስብሳቢ መዲና መሃመድ ኢብራሒም የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይልና ሕዝቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅተው በመመከት ጠላት ድል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
‘ዳጉ’ በሚባለው የመረጃ መለዋወጫ መንገድ የአካባቢው ማኅበረሰብ የጠላትን እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እያደረሱ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህም የፀጥታ ኃይሉ የጠላትን ዱካ ተከትሎ በማሳደድና በመደምሰስ የጥፋት ምኞቱ እንዳይሳካ እያደረገው መሆኑን ምክትል ስብሳቢዋ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ምክትል ኮማንደር እስማኤል አህመድ ሕዝቡ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይንበረከክ ጠላት በየገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በጀግንነት እየተዋጋ መሆኑን ገልጸዋል። ጠላት ብዙ ሠራዊት ያለውና ብዙ የታጠቀ አስመስሎ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማደናገር ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም ብለዋል።
ኮማንደር እስማኤል የአፋር ሕዝብ፣ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጠላትን በገባበት ሁሉ እየተከታተለ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ እያደረገው ነው ብለዋል። በአውደ ውጊያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና የፀጥታ አካላት ጠላት ከገባበት እንዳይወጣ ባለበት እያስቀሩት መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ