
ባሕር ዳር: ሕዳር 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋር ግንባር ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን በመፋለም ላይ ላሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሰንጋዎችን ድጋፍ አደረገ።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ሰመራ ከተማ ተገኝተው ድጋፍን ለአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድርና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዦች አስረክበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአፋርና አማራ ክልሎች የከፈተውን የግፍ ወረራ ለመቀልበስ መከላከያና ልዩ ኃይሎች እያደረጉት ባለው ከፍተኛ ርብርብ ድል እየተመገበ ይገኛል ብለዋል።
የአፋር ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ መስመር በመቆጣጠር ሀገር ለማፍረስ የወጠነውን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ከፍተኛ ጀብድ መፈጸሙን ከንቲባዋ ተናግረዋል። ለተመዘገበው ጀብድ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ሕዝብ ከፍተኛ ኩራት የተሰማቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለሠራዊቱና ልዩ ኃይሉ ያለውን አጋርነት ለመግለጽ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 120 ሰንጋዎችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አወል አርባ “ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል እና ከጀርባው የተሰለፉ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የወጠኑት ሴራ በሕዝቦቿ የተባበረ ክንድ እየተመከተ ይገኛል” ብለዋል። ከመከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል በተጨማሪ ሕዝቡ አካባቢውን በመጠበቅና ጠላትን መፈናፈኛ በማሳጣት ትልቅ ገድል እየፈጸመ መሆኑን ርእሰ መሥተዳድሩ አስታውቀዋል። ለሕይወቱ ሳይሳሳ ለሀገርና ለሕዝብ ደኅንነት እየተዋደቀ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊትና የክልሎች ፀጥታ መዋቅር ሕዝቡ እየሰጠ ያለው ደጀንነትም ለድሉ መፍጠን የጎላ ሚና እንዳለው ነው ያመላከቱት። አቶ አወል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፋ በክልሉ፣ በሀገር መከላከያና ልዩ ኃይል ስም አመሥገነዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል እሸቴ በሪሁን ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅና የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በሀገር ላይ የፈጸመውን ክህደት፣ ግፍና ወረራ በአጭር ጊዜ በመቀልበስ የወራሪውን ግብአተ መሬት ለመፈጸም በቁርጠኝነት እየተፋለመ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ