
ሕዳር 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ኃይል ወረራ በመፈፀም ሀገርን ለመበተን፣ ሕዝብን አንገት ለማስደፋት እየተውተረተረ ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይበጀኛል ያለውን ኹሉ በማድረግ ላይ ነው። አሸባሪው የትግራይ ኃይል ኢትዮጵያን ከነብሱ አስበልጦ በሚወደው የአማራ ሕዝብ ላይ ወረራ ፈፅሟል። ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎችም በርካታ በደሎችን ፈፅሟል። የሽብር ኃይሉን ሀገር የማፍረስ መፍጨርጨር ለመቋጨትና ግብዓተ መሬቱን ለማፋጠን ሀገር ወዳድ ጀግኖች እየተፋለሙት፣ መቃብሩንም እያቀረቡለት ነው። የሽብር ኃይሉን አከርካሪ እየሠበሩ ከሚገኙ ጀግኖች መካከል አንዱ የአማራ ልዩ ኃይል ነው። የአማራ ልዩ ኃይሉም ጠላት በገባባቸው አካባቢዎች ኹሉ እየደመሰሰው ነው።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ልዩ ኃይል የጣና ክፍለ ጦር አባላት ጠላትን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ወደፊት እየገሰገሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ረዳት ሳጅን ደጀኔ ገብረሃና በአማራ ክልል የገባውን ጠላት ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ ሙሉ ዝግጅትና አቅም እንዳላቸው ተናግሯል። ጠላት ከእኛ እግር ሥር እንጂ ከእኛ በላይ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለምም ብሏል። በሥነ ልቦና እና በተለያዩ ግንባታዎች በብቃት የተገነባ ሠራዊት መሆኑንም ገልጿል። ጠላትን እንቀጣዋለን ነው ያለው።

“ከሠራዊቱ የሚጠበቀው ጀግንነት እና ድል ብቻ ነው ፤ ማንኛውንም ምሽግ ሰብሮ የመግባት ብቃት ያለው ነው፤ ከዚህ ሠራዊት የሚጠበቀው አሸናፊነት እና ድል ብቻ ነው” ሲልም ገልጿል። ሠራዊቱ በተለያዩ ግንባሮች አመርቂ ድሎችንና ጀብዱዎችን መፈፀሙን የተናገረው ረዳት ሳጅን ደጀኔ አሁንም በገባንበት ግንባር አመርቂ ድል እንደምናስመዘግብ ቃል እንገባለን ብሏል።
ምክትል ሳጅን ሙሉ ብርሃን ጦሩን የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ተቆርጦ መነሳቱን ተናግሯል። ጠላትን በመደምሰስ ሀገርን ነፃ ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውንም ገልጿል።
“ጦሩ በኹሉም ነገር ሙሉ ነው፤ ወደፊት ገብተናል። ጠላትን እንደመስሰዋለን፤ ድሉም የእኛ ነው፤ በሙሉ ልብ ድሉ የእኛ ነው፤ ዛሬም ነገም አሸናፊ ነን ፤ እናሸንፋለን” ነው ያለው።
ማኅበረሰቡ በድጋፍ እንዳልተያቸው ገልጿል።

ሳጅን ደረጀ ዘውዱም የአማራ ልዩ ኃይል በልበ ሙሉነት፣ በጀግንነት እና በሞራል የተገነባ የአባቶቹን ጀግንነት አሁን ለመድገም የተነሳ፣ መንፈሱም፣ ልቡም ቆራጥ የሆነ ሠራዊት ነው ብሏል።
“ጠላት እስከ ገባበት ገብተን ድምጥማጡን እናጠፋዋለን” ነው ያለው።
ጠላት ከአሁን በፊት ከእነርሱ ጋር በገጠመባቸው አውደ ውጊያዎች ሙት እንዳደረጉት ያስታወሰው ሳጅን ደረጀ በእርግጠኝነት አሁንም እንደግመዋለን፣ ከበፊቱ የበዛ ሙት እናደርገዋለን ብሏል።
የአማራ ሕዝብ በእኛ ሊኮራ ይገባል፣ ወደፊትም ይኮራል፣ እስካሁንም እየኮራ ነበር፣ ወደፊት የበለጠ እናኮራዋለን፣ የአማራ ሕዝብ ከዚህ በኋላ አይደፈርም፣ አይፈናቀልም፣ ሀብትና ንብረቱን አያጣም፣ ሕዝባችን ከእኛ ምርጥ ድል ይጠብቅ፣ ጠላትን እንቀብረዋለን ነው ያለው።
ኮንስታብል ብርቱካን ተክለሃይማኖት ጠላትን ለመደምሰስ ቆርጠን ተነስተናል፣ የሀገራችን ሰላምም እንመልሰዋለን ብላለች። እኛ ሞተን የሕዝባችን ስቃይ ይቆማል፣ እንባው ይጠረጋል ነው ያለችው። ከዚህ በኋላ ለጠላት የሚሰጥ ምንም አይነት እድል አለመኖሩንና የመጨረሻው ትግል መሆኑንም ገልፃለች።
ጠላት ተሸንፎ ኢትዮጵያ ሰላም እንደምትሆንም ተናግራለች።

የጣና ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ እንደተናገሩት በአጭር ጊዜ ድል እናስመዘግባለን፤ ይህ ደግሞ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል። ክፍለ ጦሩ ጠላት ለምን ከመሬታችን ውሎ ያድራል? የሚል ስሜት እንዳለውም ገልጸዋል። ክፍለ ጦሩ በተሰለፈበት አውደ ውጊያ ኹሉ ድል የሚቀዳጅ መሆኑንም አንስተዋል።
ሕዝቡም በማዕበል መነሳቱን የተናገሩት አዛዡ ስንቅ በማቀበልና ከሠራዊቱ ጋር ግንባር በመሰለፍ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሕዝቡ ተነሳሽነትና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
