
ሕዳር 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ግፍ ሲመረው መገፋት ሲሰለቸው፣ በቃኝ ያለ ዕለት መውጫ ቀዳዳ ይጠባል፣ የት ልግባ ያስብላል፣ ተገፍቶ ከተነሳ፣ ነፍጡን ካነሳ የሚመልሰው የለምና። ጀግና ይታገሳል እንጂ አይቸኩልም፣ ለግፍ እንጂ በግፍ አይዘምትም። ታግሶ ሲነሳ ጠላት እንደማቆምለት፣ ምሽግ እንደማይቆይለት፣ ጥይት እንደማይባክንበት ያውቀዋልና። ትዕግሥት የጀግኖች ናት ይላል። የገፉት፣ ያዳፉት፣ በግፍ የዘመቱበት አማራ የትዕግሥት መጠኑ አልቋል፣ የመቻል ጊዜው ተጠናቅቋል፣ በቃኝ ብሏል፣ ትጥቁን አጥብቋል፣ ስንቁን ሠንቋል። አተኳኮስ በእኔ ያምራል፣ ዓልሞ መምታት ለእኔ ይቀርባል፣መዝመትም ለእኔ ይገባል ብሎ ተነስቷል።
❝እንዲህ ወደ አማራ ግፋፎ አትጣሉበት፣
ረመጡ አይለቅም ጀግኖቹ ያሉበት❞ እያለ በምሬት፣ በጀግንነት፣ በቁጭት ፣ በአይደፈሬነትና በአሸናፊነት መንፈስ እየተመመ ነው። በአማራ ምድር ግፋፎ አትጣሉበት፣ ረመጡ ይፋጃል፣ የጀግኖቹ ክንድ ያቃጥላል፣ አፈሙዛቸው ይነጥላል። ምድሩ ጀግና መፍጠር፣ ጠላትን መቅበር ያውቅበታልና። ማዕበል ሆነን እናጥፋህ ያሉትን ማዕበል ሆኖ ሊያጠፋቸው፣ በአንድነት ሊቀጣቸው፣ ከትዕግስት ወሰኑ በኋላ ያለውን ባሕሪውን ሊያሳያቸው፣ አተኳኮስ ሊያስተምራቸው፣ ክንዱን ሊያቀምሳቸው፣ ተቆጥቶ ተነስቷል።
❝ጠላት ከወረረን ከተደፈረ ሀገር፣
እንግዲህ ተነሱ ወንዙን እንሻገር፣
አቅምሰው በበልጅግ ምታው በዲሞፍተር❞ እያለ ወንዙን እየተሻገረ፣ ጋራውን እያቆራረጠ ጠላት ወደሚገኝበት ሥፍራ እየገሰገሰ ነው።
ትጥቃቸውን አጥብቀው ስንቃቸውን ሰንቀው ታሪክ ሊሠሩ ከዘመቱት ጀግኖች ጋር ተገናኝቻለሁ። አረጋ ባንቴ ይባላሉ። ከጎጃም ተነስተው ወደ ወሎ ዘምተው ወሎ ላይ ነው የተገናኘነው። እንደስማቸው እርግት ያለ ነው ባሕሪያቸው። ግርማቸው ለወዳጅ ደስ ደስ ይላል፣ ለጠላት ያሸብራል። 58 ዓመታቸው ነው። ቀዬ ተደፈረ ወገን ተወረረ ሲባል ነው ነፍጣቸውን አንስተው የሄዱት።
❝ እኔ ከዚህ ቀደምም 27 ዓመት ሙሉ በጫካ፣ በዱር ነው የኖርኩት፣ በሬዬ ታርዶ ተበልቷል። ንብረቴ ተወስዷል። ከደጄ ድረስ ሲዋጉኝ የኖሩትን ከደጃቸው ድረስ ሄጄ ለመውጋትና ልካቸውን ለማስገባት ነው በቁርጠኝነት የተነሳሁት❞ አሉኝ።
ጀግናው ቁጭት አለባቸው። ለዓመታት የበደሉት አልበቃ ብሎ ለዳግም በደል ሲመጡ አይሆንም ብለው መነሳታቸው ግፋቸው ስለመረራቸው ነው። የወገን በደል ስለበዛባቸው ነው። ❝ታሪክ ለልጆቼ ለማስረከብ፣ የእኛ አባት በዚህን ጊዜ እንደዚህ አድርጎ ነፃ አውጥቶናል እንዲለኝ ነው የመጣሁት❞ ነው ያሉኝ። አሸባሪው ትህነግ ስልጣነ መንበር እንደያዘ አካሄዳቸው ያልተመቻቸው አረጋ አሻፈረኝ ብለው ወጡ። እነርሱ ተመልሰው ጎሬ ውስጥ እስኪገቡ ድረስም ለነፃነት ዋጋ እየከፈሉ በዱር መኖራቸውን አስታውሰዋል። የአሸባሪው ትህነግ የስልጣን ዘመን ሲጠናቀቅ ነፃነታቸውን ማግኘታቸውን የተናገሩት ዘማቹ አረጋ ዛሬም ለነፃነት ስል ነው የመጣሁት ብለውኛል።
❝ጠላት እስከመጨረሻው መደምሰስ አለበት። ጠላት ከገባበት ገብተን፣ እኛም ብንሞት ልጆቻችን እየተተኩ ትግሉ መቋረጥ የለበትም። የሃይማኖት ተቋማት እየተቃጠለ፣ መጫት እየተገደለች ፣ ሴቶች እየተደፈሩ እኛ ልንቀመጥ አንችልም❞ የጀግናው ቃል ነው።
ወደ ዘመቻ መምጣት የማይችለው በገንዘብ እየረዳ፣ ቤተሰቦቻችንን አይዟችሁ እያለ ግፋ በለው ማለት አለበት ነው ያሉኝ።
አንድ እንሁን፣ መከፋፋል አይገባም፣ አንድ ኾነን የቀደሙ አባቶቻችን ታሪክ ለልጆቻችን ማውረስ አለብን፣ ልጆቻችንም ከእኛ ወርሰው መኖር አለባቸው ብለዋል።

❝ሰው ይሞታል ታሪክ ግን አይሞትም። እኔ ብሞት ልጄ መጥቶ ይዋጋል። አደራዬ ይሄ ነው❞ ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላኛው የ62 ዓመቱ ዘማች ይልቃል አሰጌ የጠላት ግፍ አንገሽግሿቸው፣ እምብኝ ብለው ተነስተው በወሎ ግንባር ያገኘኋቸው ጀግና ናቸው። ቁጭት ከፊታቸው ይነበባል። እንደሰማቸው የላቀ ታሪክ ሊሠሩ ተነስተዋል። ❝እኔ ቁጭት አለኝ። እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ሲያለቅሱ ሳይ አንጀቴ እርር ይላል። ትልቅ ነኝ። ነገር ግን ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን እየተሰቃዩ ከቤት መቀመጥ የለብንም በሚል ነው የመጣሁት። ጠላቶቻችን አንድነታችን እንዲጠናከር፣ አንድ እንድንሆን አድርገውናል። በዘር በሃይማኖት የበታተኑት አንድ ሆኗል። በአንድነት ወጥቷል፣ ጠላታችንን ድምጥማጣቸውን አጥፍተን መምጣት አለብን ብዬ ነው በቁጭት ተነስቼ የመጣሁት❞ ብለውኛል።
ዘማቹ የጠላት ግፍ እልህ አሳይዟቸዋል። ልባቸውን አሸፍቶታል። ❝አማራ አንድነቱን አጠናክሮ ጠላትን መደምሰስ አለበት፣ እኛም እንደ አባቶቻችን ጠላትን መትተን ስማችን ይጠራ፣ እኛ ሞተን ልጆቻችን ያልፍላቸዋል፣ ድሮ በአባቶቻችን ያልተደፈረች ሀገር በእኛ ጊዜ ልትደፈር አትችልም። ልጄ አንተ ደክሞሃል አትሄድም መሣሪያህን ስጠኝና እኔ ልሂድ አለኝ። አትሄድም እኔ ለአንተ ነፃነትን አውርሼ ነው የምሞተው። አንተ ከእኔ በፊት እንድትሞት አልፈልግም። እኔ ከሞትኩ ትገባለህ አልኩት❞ የዘማቾቹ ፅናትና ቃል ነው። ወደ ኋላ ላይመለሱ ቆርጠው መነሳታቸውንም ነግረውኛል።
በታርቆ ክንዴ
ወራሪውን ጠላት ደምስስ!
የጀግንነት ታሪክህን ዳግም አድስ!
ነፃነትህን አትስጥ!
ተዋርዶ ከመኖር በክብር መሞት ይሻላል!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
