
መስከረም 14/2011 ዓ.ም ማለዳ 12:00 ነበር መነሻችን ከባሕር ዳር በማድረግ ጉዟችን የጀመርነው፡፡ ጉዞ ወደ ግሸን፡፡ ግሸን ላይ ለሚከበሩት የመስቀል እና የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል የዘገባና ቀጥታ ስርጭት ሽፋን ለመስጠት ነው ጉዞዬ፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ከሙሉ የሥርጭት ቡድኑ አባላት ጋር ነው ጉዞዬ፡፡
ከባሕር ዳር ተነስተን፣ የደቡብ ጎንደርን ቀዝቃዛማ አየር እየቀዘፍን፣ የጨጨሆን ጠመዝማዛማ፣ ተራራማ እና ገደላማ መልከዓ ምድር አልፈን ለምሳ ከሰሜን ወሎዋ ጋሸና እረፍት አደረግን። ወደ ግሸን ለመሄድ ሁለት አማራጮች አሉን። አንደኛው በወልዲያ – ደሴ ገብተን 82 ኪሎ ሜትር ወደ ምዕራብ ተመልሰን ግሸን መድረስ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኮን – ደላንታ አድርጎ ግሸን መግባት። እኛም የርቀቱን አዋጭነት አስልተን የደላንታ መስመር መረጥንና ጊዜያዊ ስንቅ እንደ ውኃ፣ ብስኩትና ቆሎ የመሳሰሉትን ገዛዝተን ጉዟችን ቀጠልን።
የኮን – ደላንታ ሰንሰለታማ መልከዓ ምድር ከተከናነበው የመስከረም የአደይ አበባ ውበት ጋር ተዳምሮ ልብን ይሰርቃል፡፡ መስመሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱ ባልደረቦቼ በጠመዝማዛነቱ እና ገደላማነት ልባቸው እየራደም ሐሴት እያደረገም ጭውውታችን እና ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ ከ100 ኪሎ ሜትር ጉዟችን ውስጥ 90 ኪሎ ሜትሩ ጠጠርና አስቸጋሪ ነው፡፡ ከደሴ – ደላንታ – ኮን የአስፓልት መንገድ እየተሰራ እንደሆነ በጉዟችን ታዘብን፡፡ ከጉዟችን 10 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ እንደሄድን ‹ቆላዲ› ከምትባለው መገንጠያ አንስቶ የ17 ኪሎ ሜትር የግሸን ደብረ ከርቤ መዳረሻ ጠጠር መንገድ ገጠመን። ግሸን ለመድረስ ብዙዎቻችን ጉጉታችን ጨመረ፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የኃይማኖቱ ተከታዮችን የያዙ ሽንጣም አውቶብሶች ወደ መገንጠያው ሲገቡ ስናይ ደግሞ ከፊታችን የድካም ስሜት ሳይሆን ፈገግታ መነበብ ጀመረ፤ ብዙዎቻችን ለቦታው አዲስ ነን እና ጉጉታችን ድካማችንን አጠፋው።
370 ኪሎ ሜትር ገደማ የፈጀው ጉዟችን ወደ መቃረቢያው ሲደርስ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተራራማ ቦታ ላይ ወደ ኋላ በመንሸራተቱ መንገድ ዘጋብን። ሰዓቱ ምሽት 1:00 ላይ ያመለክታል። የእኛን ጨምሮ ብዛት ያለው ተሽከርካሪ ባለበት ለመቆም ተገደደ። ከአንድ ሰዓት መጉላላት በኋላ መኪናው ተጎትቶ ቦታ ለቀቀ፤ ‹ተመስገን!› አልን። መኪናው ባይወጣና መንገዱ ባይከፈት ኖሮ በጣም ቅዝቃዜ ካለበት አካባቢ መኪና ላይ ለማደር እንገደድ ነበር፤ ግን መልካሙ ነገር ሆነ!፡፡
የመኪና ጉዟችንን አጠናቅቀን ከጊዜያዊ የተሽከርካሪ ሥምሪት ሰጪዎች ጋር በመነጋገር የመኪኖቻችን ማሳደሪያ አመቻቸን፤ ምን ማሳደሪያ ብቻ መሰንበቻ ጭምር እንጅ፤ ምክንያቱም በዚያው ቆይታችን ከሳምንት በላይ ነውና። በነገራችን ላይ ግሸን ደብረ ከርቤ ለመድረስ ቀጥ ያለውን መልከዓ ምድር በእግር መጓዝ አለብን፤ መኪኖቻችንን ከቦታው የሚያደርስ መንገድ የለም። እኛ ለሥራ ብዙኃኑ ደግሞ መንፈሳዊ ክብርና በረከት ለማግኘት ሲል ከቦታው ለመገኘት ከተራራው ጋር ተፋጠናል። የተራራው ላይ ጉዞ ፈታኝ ነው፤ ግን እያረፍንም ቢሆን በምሽት ወጣነው። ግሸን ደብረ ከርቤ ከመስቀለኛው ከበሩ ደረስን። ጥቂት ፈታኝ መንገድ ተጉዘንም ከቤተ ክርስቲያኗ አጸድ ደረስን፤ ስንደርስ ከምሽቱ 3:00 አልፎ ነበር። የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ወደ ማረፊያቸው እንድንገባ ጋበዙን። ከአባ ጋር ሠላምታ ተለዋውጠን ጭውውት እንደጀመርን እራት ቀረበልን። ድካም በርትቶብን ነበርና ከምግብ በኋላ በፍጥነት ወደ መኝታ ክፍሎቻችን አመራን።
ሌሊቱ እንደነጋም አካባቢውን ለመቃኘት ዕድል አገኘን፤ መታደል ነው፤ ኢትዮጵያዊ መሆን!።
ድንቅ ተአምር የተገለጠባትና የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ክፋይ የሚገኝባት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ግሸን ደብረ ከርቤ። ከ1449 ዓ.ም ጀምራም በየዓመቱ መስከረም 21 የንግሥ በዓሏ ይከበራል።
ግሸን ላይ በነበረኝ ቆይታዬ ትምብትም አለኝ፡፡
የኃይማኖቱ ተከታዮች ገና ተራራው ላይ ሲደርሱ የሃሴት ስሜት ይነበብባቸዋል። ሴቶች በእልልታ ደስታቸው ይገልጻሉ፤ ያሰቡት ተሳክቶ ተራራውን ወጥተው ከቤተ ክርስቲያኗ አጸድ ደርሰዋልና። ወደ ሥፍራው የተጓዙ የኃይማኖቱ ተከታዮች የህሊና እና የመንፈስ እርካታ እንጂ ምቹ መኝታ ያለበት ማረፊያ ቤት አያገኙም፤ ይልቁንም ከአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያና በዙሪያው ካለው ሜዳ ላይ ከቤታቸው ካመጡት አልባሳት አልያም ከአካባቢው በመግዛት ጊዜያዊ ማረፊያቸውን ያዘጋጃሉ እንጅ። ዝናብና ብርዱን በጸጋ ይቀበላሉ፤ ሥርዓተ ቅዳሴውን ይከታተላሉ፤ የምሥጋናና ዝማሬንም በኅብረት ያሰማሉ።
አካባቢው ላይ መገኘታቸው ዓለማዊውን ሕይወት ለቀናት እንዲረሱና መልካምና ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲያስቡ እንደሚያደርጋቸውም ምዕመናኑ ነግረውናል። የመስቀልና የግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓላት ከሃይማኖታዊ እሴታቸው ባለፈ በጊዜያዊነትም ቢሆን ለአካባቢው የሞቀ ግብይት እንዲኖር አድርገዋል፡፡ ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት የንግዱ ማኅበረሰብ የተሳተፈበት የጦፈ ንግድ በአካባቢው ይስተዋላል። ይህ ለሸማቹም ለነጋዴውም መልካም አጋጣሚ ነው።
የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓልን ለመታደም የተገኘ ሰው ብዙ ሰብዓዊ አገልግሎቶች ይጠብቁታል። ወጣቶች ባዋቀሩዋቸው ማኅበራት አማካኝነት ምዕመኑን በተለያዬ ዘርፍ በበጎ ፍቃድ ያገለግሉታል። ከግሸን መዳረሻ ድረስ ሕዝቡን ማስተናገድ፣ ዕቃ ተሸካሚ ወጣቶችን ማመቻቸት፣ ቦታዎችን መጠቆምና ማረፊያ ማመቻቸት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መገለጫ ነው። ከሥፍራው የተዘጋጁ መጸዳጃ ቤቶችንም በየሰዓቱ በማጽዳት ምዕመኑን በቅንነት ሲያገለግሉ ተመልከቻለሁ፡፡ ይህ ከራስ መልካምነት በመነጨ ደግነት የተከናወነ ተግባር ነው፡፡
ግሸን ደብረ ከርቤ የጥንታዊ ቅርሶች ባለቤትና የጎብኝዎች መዳረሻ ከሆኑት የኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ ተቋማት መካከል አንዷ ብትሆንም በመሠረተ ልማት አልተደገፈችም። ምቹ መንገድ የላትም፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አልተሟላላትም። ይህም ለመንግሥትም ሆነ ለግል ባለሀብቶች የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡
ይህ የግሸን ጉዞና ቆይታ ትውስታና ትዝብቴ ነው፤
ስማቸው እሸቴ ነኝ፡
ቸር እንሰንብት!