ከደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት የተላለፈ መልዕክት!

443
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የህልውና ዘመቻውን በውጤታማነት ለመምራት እና አንዳንድ ለህልውና ዘመቻው እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለማረም ይረዳ ዘንድ የከተማችንን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በከተማችን የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በሚገባ በመገምገም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን አዋጅ በተደራጀ መንገድ ለመፈፀም ይረዳ ዘንድ ኅብረተሰባችን በአግባቡ ተረድቶ በአስገዳጅነት እንዲፈጽማቸው የሚከተሉትን አስገዳጅ ውሳኔዎች አስቀምጧል፡፡
የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ቀጥሎ የተዘረዘሩ ውሳኔዎችን በመፈፀም ከተማችንን ብሎ ህዝባችንን ከገጠማው የህልውና አደጋ የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ስንል ከታላቅ አደራ ጋር እንጠይቃለን፡፡
1. በማንኛውም ቦታና ሰዓት ጠላትን በማጀገን የወገንን ኃይል ሞራል የሚጎዳ፣ የመከላከያችንን፣ የልዩ ኃይላችንን፣ የሚሊሻ እና የፋኖን እንዲሁም የሕዝባችንን ክብርና ሞራል የሚነካ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እና የአሉባልታ ወሬ በመንዛት ሕዝባችንን ማሸበር ፍጹም የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን በሚያደርግ ግለሰብም ይሁን ቡድን ላይ የፀጥታ ኃይሉ እርምጃ ይወስዳል፡፡
2. በከተማችን ውስጥ የትኛውም ቦታ በየትኛውም ሰዓት ጫት በሚቅም እና በሚያስቅም እንዲሁም ሺሻ በሚያጨስና በሚያስጨስ ላይ የፀጥታ ኃይሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እርምጃ ይወስዳል፡፡
3. ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ቡድን የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አባላት ለጠየቁት መረጃም ይሁን ማንኛውም ድጋፍ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
4. ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ቡድን መንግሥት ላቀረበው የህልውና ዘመቻ ተባባሪ የመሆን ግዴታ አለበት፡፡
5. ሁሉም የከተማችን ነዋሪ በቀበሌ እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚገኝ የፀጥታ አካል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከተማውን እና አካባቢውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ሁሉም ነዋሪ የውጭ መብራት ማውጣት አለበት፡፡ ይህንን በማያደርግ ማንኛውም አካል ላይ በየደረጃው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እርምጃ ይወስዳል፡፡
6. ሁሉም የከተማችን ነዋሪ በግቢው፣ በሆቴሉ ወይንም በማንኛውም የግል ቤት እና ድርጅቱ ያከራያቸውን፣ በፈቃዱ በነጻ እንዲኖሩ የፈቀደላቸውን ግለሰቦቹን፣ ቡድኖችን ማንነት የሚገልጽ መረጃ አደራጅቶ ለቀበሌ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አባላት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ለዚህ ተባባሪ የማይሆን አካል ላይ የሕግ እርምጃ ይወሰዳል፡፡
7. ከተፈቀደላቸው ሰዎችና ተሸከርካሪዎች ውጭ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ይህን ተላልፎ በሚገኝ አካል ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል፡፡
8. ስምሪት ከተሰጣቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ውጭ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡
9. ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ፀጉረ ልውጥን መከታተል፣ መጠቆም እና ለሕግ አካሉ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡
10. ሁሉም የከተማችን ነዋሪ ራሱን፣ አካባቢውን፣ ከተማውን ከተራ ሌባ፣ ከሰርጎ ገብ እና ህልውና ላይ አደጋ ከሚያደርስ ማንኛውም አካል የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡
11. በራስ እንዝላልነት የተሽከርካሪንም ኾነ የእግረኛን እንቅስቃሴ ሊያስተጓጉል የሚችል መንገድ መዝጋትም ኾነ ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ ማቆም በሕግ ያስቀጣል፡፡
12. ከሙያው ባለቤት ውጭ የኾነ ማንኛውም ግለሰብ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይል፣ የፖሊስ እና የሌሎች የመንግሥት የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ ለብሶ የተገኘ አካል ተጠያቂ ይሆናል፡፡
13. ማንኛውም ያልተመዘገበ የትክሻ ትጥቅ ያለው አካል ከሕዳር 01/2014 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 5 ቀናት ውስጥ እንዲያስመዘግብ ተወስኗል፡፡ ከሕዳር 5 በኋላ በፀጥታ አካሉ ፍተሻም ይሁን በጥቆማ የተገኘን የትክሻ መሳሪያ ወደ መንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡
14. ያለ ምክንያት ጥይት መተኮስ ክልክል ነው፡፡ ያለ ምክንያት የተኮሰ ግለሰብ ትጥቁ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡
15. ከኮማንድ ፖስቱ እውቅናና ፈቃድ ውጭ ስብሰባ ማድረግ፣ ሀብት መሰብሰብ፣ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ያስጠይቃል፡፡
ሁሉም አካል ቀደም ሲል የተገለጹትን ግዴታዎችን በመወጣት እና ያልተወጡ ግለሰቦችን ለሕግ አካሉ በመጠቆም ትብብር እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡
ለጋራ ህልውና በጋራ እንዝመት!!!
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፀጥታ ኮማንድፖስት
ሕዳር 2/2014 ዓ.ም
Previous article❝እሳተ ነበልባሉ የጫካው አንበሳ፣ ሀገር ብትጠራው ምቾት ይቅር ብሎ ፎክሮ ተነሳ❞
Next articleዓለም አቀፍ ተቋማት እና ድርጅቶች የኢትዮጵያን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አክበረው መንቀሳቀስ አንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡