
ሕዳር 01/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕረስ ሴክሬተሪ ብልለኔ ስዩም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ ከሲ ኤን ኤን ጋር በነበራት ቆይታ ❝ሲ ኤን ኤንን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያሰራጯቸው ዘገባዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳዩ አይደሉም❞ ብላለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ተገቢ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግራለች።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከሽብር ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች በሕግ ተጠያቂ ለማድረግና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚደረገውን ተግባር ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ኾን ተብሎ የትግራይ ተወላጆችን በማንነታቸው ለማጥቃት የተደረገ አድርገው ማስተጋባታቸው እጅግ ከእውነታ የራቀና አሳፋሪ ተግባር መሆኑንም ጠቅሳለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ሰላም በሚል የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማድረጉን ተከትሎ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና በአፋር የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙንም ገልጻለች። በዚህም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን አስታውቃለች።
መንግሥት ያደረገውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ ለትግራይ ሕዝብ ብሎ ያደረገው መሆኑን አንዳንድ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን አለመግለጻቸውንም ጠቅሳለች።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ ምርጫ በማከናወን መንግሥቷን መመስረቷንም ተናግራለች።
ዘጋቢ:- ፈረደ ሽታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ