
ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ንጹሐን አማራዎች ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በአሸባሪው ትህነግ የተጨፈጨፉበት ዕለት አንደኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት በማይካድራ ታስቦ ውሏል።
የማይካድራ ነዋሪዎች አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ድርጊት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አሸተ ደምለው ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ባለፉት 30 ዓመታት ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ጆሮ የነሳውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ፈጽሟል ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በማይካድራ ባካሄደው ጭፍጨፋ ከሟቾቹ ባለፈ 1 ሺህ 644 ነዋሪዎች ለሥነልቦና ቀውስ ተዳርገዋል፤ 81 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 1 ሺህ 563 በላይ ሰዎች ደግሞ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
አቶ አሸተ እንዳሉት በማይካድራ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መርምሮ በድርጊት ፈጻሚዎቹ ላይ ክስ በመመስረት ፍትሕ እንዲሠጥም ጠይቀዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አማራ ተወላጆች ለደረሰባቸው ማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዲሁም ለተፈጸመባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል በደረሰው ጉዳት እና በተፈጸመው ልክ ካሳ እንዲከፈልም ነው የጠየቁት፡፡
አቶ አሸተ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን ለቀጣናው ጭምር ስጋት በመሆኑ እሱ ከሚመራው መንጋ ጋር ከነአስተሳሰቡ ወደ መቃብር እንዲወርድ የህልውናና ሀገር የማዳን ተጋድሎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው እንደገለጹት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል አፓርታይዳዊ አገዛዝ ከዘረጋ ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽም ቆይቷል፤ ማሳያውም ከሁመራ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ የጅምላ መቃብር እስከ ማይካድራ ጭፍጨፋ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በየዋሻው ውስጥ የተገኙ መቃብሮች በጅምላ ያለቀው ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው ብለዋል፡፡
የማይካድራ ጭፍጨፋ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአገዛዝ ዘመኑ በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም የቆየውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ግልጽ ማሳያ መሆኑን አቶ አሸተ ጠቁመዋል፡፡
ዋና አስተዳደሪው ሕዝቡ ቡድኑን ለመፋለም ቆርጦ መነሳቱንም ነው የገለጹት፡፡
በወቅቱ ልጆቻቸው እና የትዳር አጋሮቻቸው የተገደሉባቸው እና በሰልፉ የተሳተፉ የማይካድራ ነዋሪዎች ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ ጭፍጨፋ ፈጽሞብናል ነው ያሉት፡፡ ይህንን ዘርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ የፈጸመ እና እየፈጸመ ያለውን ወራሪ ኃይል ከነአስተሳሰቡ ለመቅበር ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ልጆቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን መከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኀይልን እንዲቀላቀሉ ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ለመደምሰስ በቁርጠኝነት መነሳታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ምሽት ላይ ሰማዕታትን የሚዘክር የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ -ከማይካድራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ