
ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በደም የተቀረፀ ማሕተም ያረፈባት፣ የደም ቃል ኪዳን የተተወባት፣ የንጹሐን ድምፅ የሚታወስባት የትውልድ አደራ። ልርሳህ ቢሉት የማይረሳ፣ ከልብ መዝገብ ላንሳህ ቢሉት የማይነሳ የደም ቃል ኪዳን። መኖር ተመኝተዋል። ለሕይወት ጓጉተዋል። እቅድ ነድፈዋል። ተስፋ ሰንቀዋል። ዳሩ ተስፋቸውን፣ ሕይወታቸውን እቅዳቸውን በክፉዎች በትር ተነጠቁ። በግፍ በትር በግፍ አለቁ። የማይካድራ ጎዳናዎች በደም ራሱ፣ ሕጻናት ወላጆቻቸውን ተነጥቀዋልና ምርር ብለው አለቀሱ። የግፍ ፅዋ ፈሰሰ ፣ በከተማዋ ጎዳናዎች ለቅሶና ዋይታ ነገሠ። በልባቸው በደል ያልተገኘባቸው፣ በአንደበታቸው ክፉ ያልወጣቸው፣ በሥራቸው ጥፋት ያልተመዘገበባቸው ለፍቶ አዳሪ፣ ጥሮ ኗሪ የክፋት ሰይፍ በላቸው። ክፉዎች አንገታቸውን ቀሉት፣ አስክሬናቸውን በመንገድ ጣሉት፣ በሬሳቸው ላይ ቀለዱበት፣ ዘበቱበት።
አባቶቻቸው ለሰይፍ ሲዘጋጁ ያዩ ሕጻናት በጎልዳፋ አንደበታቸው፣ በንጹሕ ልባቸው፣ እንባ ከዓይናቸው እየፈሰሰ፣ አንጀታቸው እየተላወሰ አጥብቀው ለመኗቸው።
❝አባቴን ተውልኝ፣ እንወደዋለን፣ ብቻችን አታስቀሩን፣ አባት አታሳጡን፣ ማዕረጋችን ክብራችን አትንጠቁን❞ እያሉ ተማፀኗቸው። እነርሱ ግን ይተዋቸው ዘንድ አልፈቀዱም፣ የሚራራ ልብ አልነበራቸውም። ከሕፃናቱ ፊት በሠይፍ ቀሏቸው። ያለ በደል ጨከኑባቸው፣ ተስፋቸውን ነጠቋቸው፣ ዘመናቸውን የወሰዱባቸው። እንደ ቀላል ነገር ወረወሯቸው፣ ሰውን ያክል ታላቅ ፍጡር እንደዘበት ጣሏቸው። ሕጻናቱም ከእናቶቻቸው እግር ሥር ቀሚሶቻቸውን ጨምድደው ይዘው አባቶቻቸው በሰይፍ ተቀልተው ዓለምን ሲሰናበቷት እየቀፈፋቸው ተመለከቱ። እናቶቻቸውም የባሎቻቸውን ሞት በሰቀቀን ቆመው አዩ። ደራሽ አልነበራቸውም። አይዟችሁ የሚል፣ ለበቀል የተነሱትን የሚገላግል አልተገኘም። የከተማዋ ጎዳናዎች በንጹሐን አስከሬን ተሞላች፣ በቆፈን ተያዘች።
❝አቤቱ ፍርድህ ራቀ፣ የግፏን ምድር ተመልከታት፣ ደሟን አብስላት፣ እንባዋን ተቀበላት፣ የፍጥረታት ኹሉ ጌታ፣ ለተጨነቁት የምትደርስ፣ ያዘኑትን እንባ የምታብስ ለእኛም ድረስ እንጂ። ዘገየህስ፣ ፍርድህን ለምን አራቅክብን፣ ሰማይ ተደፍቶብናል፣ ምድር ጨልሞብናል፣ ተስፋችንን ተነጥቀናል፣ ጨለማ ይዞናልና እባክህን ቶሎ ና ❞ እያሉ የሚያለቅሱትና የሚማፀኑት ብዙዎች ነበሩ። ቀን ሲጨልምባቸው፣ ተስፋ ሲጠፋባቸው፣ የደም ማዕብል ሲያጥለቀልቃቸው ከፈጣሪ ሌላ ለማንስ ይነግሩታል? ለማንስ ያማክሩታል?
በመልካሙ ዘመን ያበሉ ያጠጡ፣ የተቸገሩትን ከችግር ቀን ያወጡ የዋሆች፣ ባለ መልካም ልብ ባለቤቶች፣ በክፉው ቀን ካዷቸው፣ መርገም ያልተገኘበት፣ በደል ያልተመዘገበበት ስም ሰጧቸው።
❝ክፉ ሰው በራስ ሀገር ከራስ ድግስ ያባርራል❞ እንዲሉ በራሳቸው ሀገር፣ በራሳቸው ርስት፣ በራሳቸው ጉልት፣ ያለ ማንነታቸው ማንነት ተሰጥቷቸው ኖሩ። በመጨረሻው ቀን ስም ተሰጥቷቸው፣ አማራ የሚለው ማንነታቸው እንደ በደል ተቆጥሮባቸው ከሰው አስለይቶ አስገደላቸው፣ ለሠይፍ ዳረጋቸው። በዚያች ምድር የአማራ እንባ ፈሰሰ። ሺህዎች ተገደሉ፣ ጎዳናዎች በለቅሶ ተሞሉ፣ ሰማይ ተደፋባቸው፣ አብዝቶ ጨነቃቸው ፣ አካባቢውን የሐዘን ባሕር ዋጠው፣ የንጹሐን ለቅሶ አናወጠው፣ በሰይፍ የተቀሉት ፣ በስም ብቻ ለግዳይ የቀረቡት በጭንቅ እያቃሰቱ፣ የደስታውን ዘመን ሳያዩት ተሰናበቱ።
ብዙዎች ገዳዮች አልፈው መልካም ዘመን ይመጣ ዘንድ ጓጉተዋል፣ ተመኝተዋል። ያችን ቀን ያዪዋት ዘንድ ናፍቀዋል፣ ተቻኩለዋል። ታዲያ የናፈቋትን ቀን ሳያዩዋት፣ በደስታ ሳያከብሯት በግፍ ተሰናበቷት። በማይካድራ የግፍ ግፍ ተፈፅሟል። ጨካኞች ዘር ለይተው አጥፍተዋል፣ ማንነት አስልተው ገድለዋል፣ ቀን ጠብቀው ክደዋል። ዘመን ጠብቀው የልባቸውን መሻት ፈፅመዋል። ዳሩ የንጹሐን ደም ጠራርጎ ያጠፋቸዋል፣ አርቆ ይወስዳቸዋል። የዋይታቸው ጩኸት እየተከተለ ያሳድዳቸዋል። በግፍ የተገደሉት በደል አልተገኘባቸውምና ነብሳቸው ታርፋለች፣ ንጹሐንን የገደሉት ደግሞ ስጋቸውም ነብሳቸውም ትባዝናለች። መጠጊያ ጠል ታጣለች፣ ድንጉጥ ኾና ትቅበዘበዛለች። የደም ዋጋ ትጠየቃለችና ረፍት ታጣለች።
ዓለማት ኹሉ ዝም ቢሉም፣ ጠላቶች ኹሉ በንጹሐን ደም ቢቀልዱም ማይካድራ አትረሳም። አደራዋ የደም ነውና ማይካድራ ትታወሳለች፣ ትታሰባለች። የንጹሐን ደም ይጣራሉ፣ በሐዘን የጮሁት ድምፆች፣ ዋይታ የነገሠባቸው ጎዳናዎች አትርሱን ይላሉ። ትውልዶች ኹሉ የእነርሱን ጠላቶች ይከተሏቸዋል፣ ያሳድዷቸዋል፣ በፍርድ አደባባይ ያቆሟቸዋል፣ በጨከኑበት ክንዳቸው ይጨክኑባቸዋል። የወጉት ቢረሱም የተወጉት አይረሱም። ማይካድራ በደም የተቀረፀ አደራ የተቀበሉባት፣ ወገኖቻቸውን ያጡባት ናትና አይረሷትም። ብዙዎች ከሟቾቹ ይልቅ ለገዳዮቹ አዝነዋል፣ ስለ ገዳዮቹ መብት ተከራክረዋል። ስለ ገዳዮቹ መሳደድ ጠበቃ ቆመዋል። ዓለም እውነተኞችን ካደች፣ ሐሰተኞችን ደገፍች፣ ስለ ንጹሐን ደም አንደበት አጣች፣ ስለ በደለኞች ያለ ረፈት ተናገረች። ቆማ ተከራከረች። በማይካድራ ስላለቁት ንጹሐን ግን ዝምታን መረጠች።
አቤቱ የግፍ መብዛት። ለነዚያ ንጹሐንን ከንፈር መጥጦ ማዘን እንኳን ተነፈጋቸው። እውነት በውሸት አደባባይ ቦታ የላትም። ደጋፊ አይገኝላትም። የደረሰው ኹሉ ያዋርዳታል፣ ይሰድባታል እንጂ። እውነት ግን በእውነተኛው መንገድ የእውነተኛውን አምላክ ይዛ ታሸንፋለች። አዎን ዘር መርጠው የገደሉት፣ ያሳደዱት ዛሬም ጨርሶ ምድር አልበላቸውም። ዛሬም ዘር እየቆጠሩ መግደል ማፈናቀል ተያይዘውታል። የማይካድራው ሳይበቃቸው፣ እርሱ ሳያረካቸው ዛሬም በደረሱበት ኹሉ እየለዩ ይገድሉታል።
ዘር ቆጥረው፣ ማንነት አስልተው የሚገድሉትን፣ የሚያሳድዱትን ዝም ብትላቸው የንጹሐን ደም ይወቅስሃል፣ በደም የተቀረፀ ቃል ኪዳን ተሰጥቶሃልና ግፈኞችን ከግፋቸው አስቁማቸው። በሚገቡበት ኹሉ ተከተላቸው፣ ረፍት አትስጣቸው ፣ እነርሱ ማረፍ ለሚፈልጉት እረፍት፣ መኖር ለሚፈልጉት ሕይወት አልሰጧቸውምና አንተም አትስጣቸው። በንጹሐን ደም እጁ የተጨማለቀውን፣ በጥላቻ የሰከረውን አሸባሪና ወራሪ ቡድን እንዲኖር አትፍቀድለት፣ አንድም ቀን አትጨምርለት፣ በተሰጠህ የደም ቃል ኪዳን መሠረት ዘምተህ፣ ጠላትህን መትተህ፣ ወደ አፈር ሸኝተህ፣ አደራህን ተወጣ። ❝አደራ ከሰማይ ይርቃል❞ እንዲሉ አበው የተሰጠህ አደራ ደም ያረፈበት፣ እንባ የፈሰሰበት ነውና አደራህን ጠብቅ፣ አደራህን ፈፅም።
አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ወደ ኋላ ከቀረህ፣ ካመነታህ፣ ክንድህን ካላነሳህ፣ ዐሻራህን ካላሳረፍክ ግን የንጹሐን ደም ይወቅስሃል፣ አጥንታቸው ይወጋሃል፣ ድምጻቸው እረፍት ይነሳሃል። አባቶቻቸው ሲሞቱ ከእናቶቻቸው እግር ስር የእናቶቻቸውን ቀሚስ ጨምድደው የግፍ ሞት የተመለከቱት ሕጻናት እንባ እንዲታበስ፣ ልባቸው እንዲጠገን ጠላቶቻቸውን አጥፋላቸው። ጠላትህን ዝም ካልከው ግን ሌላ ማይካድራ ይፈፅማል። በሀገርህ፣ በርስትህ ባርያ አድርጎ ያኖርሃል። በማንነትህ እያሳደደ ይገድልሃል። የተከበረውን ታሪክህን ያዋርደዋል። ትውልድህን ያመክነዋል።
እነሆ ልክ በዛሬዋ ቀን ነበር በማይካድራ ንጹሐን አማራዎች ያለቁት፣ በግፍ የተጨፈጨፉት፣ በጅምላ የተቀበሩት። የህልፈታቸውን ቀን አስብ፣ ገዳዮቹ ወዳሉበትም ትመም። ተገፍቶ መኖር፣ ተክዞ ማደር በዘሬ የለም በላቸው። ክንድህን አሳያቸው፣ በትርህን አሳርፍባቸው። አዎን ማይካድራን እንዳትረሳት ፣ ከልብህ እንዳታወጣት፣ ዘላለም አስታውሳት። ቃል ኪዳኗን ተወጣላት። ማይካድራን ከረሳሃት ታሪክ ይረሳሃል፣ ትውልድ ይታዘብሃል፣ የንጹሐን ነብስ ታዝንብሃለች፣ ትውልድ እንዲያከብርህ፣ ታሪክ እንዲዘክርህ፣ ነብሳቸው እንድትደሰትብህ ከፈለክ ዛሬውኑ ተነስ ጠላትህን ደምስስ። ምድሯን ካሳት። የማይካድራ ጎዳናዎች በደስታ እንዲሞሉ፣ በጎዳናዎቿ የሚመላለሱት እልል እንዲሉ፣ በደስታ እንዲጨፍሩ ልብህ ከወደደች ክፉዎችን ቅጣላቸው።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ