
ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጣሊያንን ወራሪ ጦር አፈር ካስገቡት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል የዋግ ሹሞቹ ደጅ አዝማች ኃይሉ ከበደ (አባ መረብ ኃይሉ) ታሪክ ሁሌም ይዘክራቸዋል፡፡
በወቅቱም “እሺ ላለው ስጠው እምቢ ላለው ንሳ፣
አባመረብ ኃይሉ የተከዜው ነብር የወለሁ አንበሳ” ተብሎ የተገጠመላቸው ጀግናው ደጅ አዝማች ኃይሉ ከበደን ኢትዮጵያ በፍጹም ውለታቸውን አትረሳውም፡፡
ዛሬም አባ መረብ ኃይሉን ያፈራ ማሕጸን ጀግኖችን አፍርቶ ጠላት ረፍት አጥቷል፡፡
ታሪክ የማያውቀው ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል ቅዠቱ በከፈተው ጦርነት ዛሬም በጀግኖች ልጆቿ እየተለበለበ ነው፡፡
ዕለቱ መስከረም 3/2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ ነው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና ከተማ ሰቆጣን ተሻግሮ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ድሃና ወረዳን ለመውረር አሰፍስፎ እየተጓዘ ነው።
በድሃና ወረዳ የቆዝባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበራው ባየ ደግሞ የጀግናው ደጅ አዝማች ኃይሉ ከበደ ሀገር እንዴት በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ወሬ ይሸበራል ብለው ጠላትን ለመፋለም የውጊያ ቦታ መምረጥ ጀመሩ። ይልቁንስ በአራቱም አቅጣጫ እየተግተለተለ ከመጣው ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር አንድ ካዝና ጥይት ይዘው ተኩስ ገጠሙ።

ብቻቸውን ሆነው ከጠላት ጋር ተኩስ የከፈቱት የድሃናው ጀግና አነጣጥረው በመተኮስ የታጠቁትን እየመረጡ ወደ ሲዖል ሸኟቸው፤ በርካቶችን ቁስለኛ አደረጓቸው። ቁስለኛ የወራሪ ኃይሉ አባላት የጀግናውን የማይጨበጥ እሳት እጅ አላወቁትም እና “እጅህን ስጥ” እያሉ ሲጮኹ ነበር፤ የአርበኛው እጅ ግን የማይያዝ ፍም ሆኖ አቃጠላቸው እንጂ፡፡
እኝህ ጀግና የያዙት ጥይት ሲያልቅ እንኳ ወደ ኋላ ከመሸሽ ይልቅ ከግዳያቸው መሣሪያ በማንሳት እንደገና ለመጨረሻ ድል ለመፋለም ይወስናሉ። እናም ወደ ወደቀው አስክሬን በመጠጋት 30 ጥይትና አንድ ክላሽ አነሱ። በዚህ ወቅት የጀግናውን ብርቱ ጥቃት መቋቋም የተሳነው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተጨማሪ ኃይል ሲያመጣ አባ ረፍርፍ አበራው ተመለከቱ።
ጀግና አበራው አሁንም ተስፋ በቆረጠ ስሜት ለሞት እየተጣደፈ ለሚመጣው ወራሪ ቡድን ሳይረበሹ 10 ጥይት እስከሚቀራቸው ድረስ እየተፋለሙ ተኩሱን አቀለጡት። ከጠላት ጥይት አንስተው በጀመሩት ውጊያም 20 ጥይት ተኩሰው 10 ብቻ ቀራቸው። አሁንም በርካቶችን ረፈረፉ፡፡
የልባቸውን ሠርተው ወደ ሚያውቁት ጫካ ተሰወሩበት፤ ያ ሁሉ ግትልትል የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል አስከሬኑን እንኳን ማንሳት ሳይችል የተረፈው ሽሽቱን ቀጠለ፡፡
እሳቸው ዱር ቤቴ ብለው አሁንም ጠላታቸውን ረፍት እየነሱት ነው፡፡
“ሀገሬ ተወራ ከተማ ገብቼ መኖር አልፈልግም፤ አካባቢዬን ጥዬ የትም አልሸሽም” የሚል የጸና አቋም አላቸው።
በጫካ በአርበኛው አበራው የደረሰበት ሽንፈት የተበሳጨው የሽብርተኛው ትግራይ ወራሪ ኃይል ወደ አቅራቢያው መንደር ገብቶ በንጹሐን ላይ የበቀል እርምጃውን መውሰድ ጀመረ፡፡ የአርሶ አደሩ የእርሻ በሬ እያረደ በላ፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ የገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከል እና መሠል ተቋማትን እና መሠረተ ልማቶችን አወደመ።

አርበኛ አበራው ከበረሃ ሆነው ይህንን ሲሰሙ እጅግ ይበሳጫሉ፡፡ ይህ ወራሪ እና አሸባሪ ቡድን መንደር ውስጥ ንጹሐን ላይ ግፍ መሥራት እንጂ እንደጀግኖች መፋለም እንደማችል በተግባር አይተዋል።
ጀግናው አበራው አሁንም ይህንን ግፈኛ ቡድን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት በቁጭት ተነሱ፤ ከቀናት የበረሃ ቆይታ በኋላ በዙሪያ የነበሩ የአካባቢውን ሚሊሻ በማሰባሰብ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ውጊያ ገጠሙት።
አባ ረፍርፍ አበራው ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ላይ በሰነዘሩት ከባድ የማጥቃት ርምጃም አሸናፊ በመሆን በአጭር ቀናት ከቆዝባ ቀበሌ እየገረፉ አባረሩት፡፡
አርበኛ አበራው ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ከሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ወደ ኋላ በማሰብ “እኔ እንኳን በ54 ዓመቴ ወራሪውን ቡድን ረፍርፌ ከፍተኛ ጀብዱ ሠርቼያለሁ፤ ሌላውም ወጣት ይህንን ማድረግ ይችላል” ብለዋል።
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል እኩይ እና ለማንም የማይመለስ አረመኔ መሆኑን ማየታቸውን የገለጹት ጀግናው አበራው ሕዝቡም ይህንን በመረዳት ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተሰልፎ በጀግንነት ሊፋለመው ይገባል ብለዋል።
አባ ረፍርፍ አበራው ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት ሕዝብን ለመፍታት እንደሚሠራ መረዳት ይገባል ብለዋል።
ጠላት የሚጠቀመውን ስልት እንደሚያውቁ የገለጹት የዛሬው የአሚኮ ጀግና ባለ ታሪክ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ከዋግኽምራ በጀግኖች ፈርጣማ ክንድ በአጭር ቀናት ይደመሰሳል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎች መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ወደ ቀያቸው ተመልሰው ከጠላት ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ እያደረጉ ነው፡፡
የተፈናቀሉ ወጣቶችም ወደ ቀያቸው በመመለስ ጠላትን ሊፋለሙ እንደሚገባቸው ጀግናው አበራው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው-ከአምደ ወርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ