አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል ለመደምሰስ ቆርጠው መሳታቸውን የፋርጣ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

206
ደብረታቦር፡ ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ወርሮ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የሽብር ኀይሉ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀልበስም ሕዝቡ በየአካባቢው ሆ ብሎ ተነስቷል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በፋርጣ ወረዳ ከጋሳይ እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡
የወረዳው ነዋሪዎችም የሽብር ቡድኑን ለመደምሠስ የድርሻቸውን ለመወጣት ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ጠላት አካባቢውን በወረረበት ጊዜ አስነዋሪ እና አሳፋሪ ተግባራትን ፈጽሟል፤ ይህ ድርጊት ዳግም እንዳይፈጸም መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለን ዘምተናል፤ ቀሪው ኅብረተሰብም ጠንካራ ደጀን በመሆን ሀገርን ከወራሪው ኀይል ለመመከት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲን ወክለው በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጉምሩክ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እባቡ ፀጋ የጋሳይና አካባቢው ነዋሪዎች በከፍተኛ ወኔ ተደራጅተው ዘመቻውን እየተቀላቀሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለያየ መድረክም የተስተዋለው ይኼ ነው፤ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ካሰማራው ገዳይ ቡድን በላቀ ደረጃ በመሰለፍ ሀገርን ነፃ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህም በቅርቡ ውጤት ያስመዘግባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አደረጃጀት ክፍል ኀላፊ ጋሻው መርሻ ሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ኀይል ለመደምሰስ የሕዝብ ማዕበል መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ጋሻው ሕዝቡ የወገን ጦርን በሥንቅ እና በትጥቅ በመደገፍ ጠንካራ ደጀን መሆን እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡
ወጣቶችም የመከላከያ ሠራዊትን እና የአማራ ልዩ ኀይልን እንዲቀላቀሉና ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አቶ ጋሻው ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ የቻለ በግንባር እንዲሰለፍ፣ ያልቻለ መሳሪያውን ለሚዘምተው አካል ሠጥቶ የማስተባበር ሚናውን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡
የአደረጃጀት ክፍል ኀላፊው ጦርነቱን ለማሸነፍ በግንባር መፋለም ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጠላት በጦር ሜዳ ገጥሞ አሸንፎ አያውቅም ነገር ግን በባንዳዎች ታግዞ በሚያሠራጫቸው ውዥብሮች ማኅበረሰቡን ግራ እያጋባ ነው ይህ ተግባሩ እንዲቀለበስም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።
አቶ ጋሻው ፖለቲካዊ ፉክክር ለማድረግ፣ እኛ የምንታገለው ዴሞክራሲ ለመገንባት ነው፤ ያለ ሰላም እና ያለ ሀገር ግን አንድ ቀን እንኳን ማደር አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ሀገርን ነፃ ለማውጣት በአንድነት እና በተናበበ መልኩ መዋጋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ “ሀገር እንድትቆም የተቻለንን ሁሉ እናድርግ” ብለዋል፡፡
አቶ ጋሻው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር የማዳን ሥራው ላይ ድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከፋርጣ ወረዳ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት ኮማንድ ፖስት የተላለፈ አስቸኳይ መልዕክት፡፡
Next articleየጠላት ማርከሻው የዋጉ ጀግና…