
በአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንደሚሠራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ካትሪን ሱዚ ገለጹ።
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ ክልል በከፈተው ወረራ በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶችን ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል፡፡ ንጹሐን የጦርነቱ ሰለባ ሆነዋል፣ ሕጻናት ሴቶች እና አረጋውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ በጊዜያዊነት ለመደገፍ እና የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከክልሉ እና ከፌዴራል መንግሥት አቅም ውጭ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ካትሪን ሱዚ ከተመራው የሰብዓዊ ድርጅቶች ልዑክ ጋር ዛሬ መክረዋል፡፡
በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ወረራ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ውይይቶች እና ጥሪ ቀርቦ እንደነበር ያወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በተግባር የተደገፈ ድጋፍ ግን የውይይቱን ያክል አልተገኘም ነው ያሉት፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳብራሩት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ዓለም አቀፍ የጦርነት መርህን በጣሰ መልኩ ንጹሐንን የጦርነቱ ሰለባ አድርጓል፣ አፈናቅሏል፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን አውድሟል፣ መሰረተ ልማቶችን ዘርፏል፤ ለዚህ ሁሉ ጉዳት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጠው ተግባራዊ ምላሽ ግን የሚጠበቀውን ያክል አይደለም፡፡
በየጊዜው ውይይቶች መካሄዳቸው፣ የጉዳቱን መጠን መረጃ መሰብሰቡ እና ተቀራርቦ መሥራቱ መልካም መሆኑን አንስተው ለችግሩ ስፋት የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ ማየት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ካትሪን ሱዚ ለችግሩ የሚመጥን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በተደጋጋሚ ቃል መገባቱን ገልጸው ርእሰ መሥተዳድሩ ያነሱት የተግባራዊ ምላሽ ጥያቄ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የጦርነቱ ሂደት መራዘም፣ የተጎጂዎች ቁጥር በየጊዜው መጨመር እና ንጹሐን የጦርነቱ ሰለባ መሆናቸው በድጋፍ አቅርቦቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ ከተፈጠረው ችግር አንፃር አናሳ ቢሆንም ሙከራዎች መኖራቸውን ያነሱት ዶክተር ካትሪን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ ድጋፍ ለማድረስ ድርጅታቸው እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት፣ የጤና እና የውኃ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድጋፍ ለማድረግ በየጊዜው መረጃ እየተሰበሰበ ነው ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡
የዓለም ምግብ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስቴቨን ዎሬ ኦማሞ በሽብር ቡድኑ በተወረሩ አካባቢዎች ላሉ እና አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረስ በኢትዮጵያ በቂ የምግብ ክምችት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ለአቅርቦቱ ችግሮች ያሏቸውን ምክንያቶች ለርእሰ መሥተዳድሩ አቅርበዋል፡፡
“በተወረሩ አካባቢዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ህወሓት እንቅፋት ሆኖብናል” ነው ያሉት ስቴቨን ዎሬ ኦማሞ፡፡
የሚላከው የምግብ ድጋፍ ቀጥታ ለተጎጂዎች መድረሱን ማረጋገጥ አለመቻሉን፣ የምግብ ድጋፉን ለማድረስ የትራንስፖርት እና የፀጥታ ስጋት ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ከፌዴራሉ እና ከክልሉ መንግሥት ጋር ተቀራርቦ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ወረራው ከተፈጸመ ጀምሮም እስካሁን ድረስ 7 ሺህ ኩንታል ምግብ በዓለም የምግብ ድርጅት አማካኝነት ቀርቧል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በየወሩ 795 ሺህ 756 ኩንታል የምግብ ድጋፍ ቢያስፈልግም ለ532 ሺህ 106 ተፈናቃዮች 79 ሺህ 816 ኩንታል ምግብ እየቀረበ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካትሪን ሱዛን እና ልዑካቸው በዘንዘልማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m