
ጎንደር፡ ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር የህልውና ዘመቻውን አስመልክቶ በዞኑ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያውን የሰጡት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያም አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይል በአማራ ክልል ተራሮችና ሸለቆዎች በተለይም ወቅን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደ አንበጣ መንጋ መርገፉን አስታውሰዋል።
“በታሪክ የውጪ ወራሪዎች ፊት ለፊት ገጥመው ማሸነፍ ስላቃታቸው ዛሬም በባንዳዎቹ ቢመጡም እንደ ጥንቱ አይሳካላቸውም፣ መዋረዳቸውም አይቀርም” ብለዋል።
አቶ ወርቁ እንዳሉት ጠላትን ለመቅበር የዞኑ ሕዝብ ሴት፣ ወንድ፣ አዛውንት፣ ሳይል ጠላትን ለመቅበር በሕዝባዊ ማእበል ከጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀስ ወደ ግንባር እየተመሙ ነው። አስተዳዳሪው ሁሉም ሕዝብ ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ በመሆኑ ከፊሉ ሕዝብ ሰብል እንዲሰበሰብና በወረፋ እንዲዘምትም መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል። ቀሪው ማኅበረሰብ የዘማቹን ሰብል እንዲሰበስብ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ወርቁ የዞኑ ሕዝብ የዘማች ልጆች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ዘመቻውን እየደገፉ እንደሆነም አስረድተዋል።
የዞኑ ሕዝብ ወራሪው ቡድን ቀየው ድረስ እስኪመጣ አለመጠበቁን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በየ አውደ ግንባሩ በመዝመት ግዴታውን መወጣቱን አስታውሰዋል።
ዘመቻውን ለመደገፍ ሴቶችና እናቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ስንቅ እያዘጋጁ ደጀንነታቸውን እያሳዩ መኾኑንም ተናግረዋል። በስንቅ ዝግጅቱ ተማሪዎች ሳይቀር የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደኾነም አመላክተዋል።
በዞኑ የሚገኙ ኹሉም የሥራ ኀላፊዎች ከዘማቹ ጋር በመዝመት የመሪነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወርቁ ቀደሞ በነበረው ትግልም መሪዎቹ አኩሪ ጀብድ መፈጸማቸውን ጠቅሰዋል።
ለመዝመት ተራውን የሚጠብቀው ቀሪው ኅብረተሰብም የውስጥ ደኅንነትን በመጠበቅ ደጀንነቱን እያስመሰከረ እንደኾነ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በየአካባቢው የተጠናከረ የኬላ ፍተሻ በመኖሩ በጠገዴ ወረዳ በርካታ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል። ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የተደራጀ ኀይል መኖሩንም አስገንዝበዋል።
የነበረውን ተሞክሮ በመቀመር የጠላት ትልቁ መሳሪያው የኾነው የማደናገሪያ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ስለኾነ ከወዲሁ ለማክሸፍ ለኅብረተሰቡ በየ መድረኩ በቂ ግንዛቤ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ