
ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል በአጭር ጊዜ በማጽዳት ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የድል ብስራት እንደሚያሰሙ በጋሸና ግንባር ተሰልፈው ጀብድ የፈጸሙ የሠራዊት አባላት ተናግረዋል፡፡
በግንባሩ የተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጋር በቅንጅት በፈጸመው ጀብድ አሸባሪውን ኀይል ድባቅ በመምታት ቀቢጸ ተስፋውን መና አስቀርቷል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ከጦርነት ሕግ ባፈነገጠ መልኩ ንጹኃን በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ፈንጂ በማጥመድ ለአማራ ሕዝብ ያለውን የጥላቻ ጥግ አሣይቷል፡፡ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የሠራቸውን ምሽጎች በፈንጂ ቢያጥርም የሠራዊት አባላቱ በሰለጠኑት ወታደራዊ ስልት ፈንጂዎችን በመጥረግና በመጠቅጠቅ ታላቅ ጀብድ ሠርተዋል፡፡

ከጋሳይ እስከ ደብረዘቢጥ የጠላት ምሽግ ሲሰበር አስር አለቃ በቀለ እሸቱ፣ አቡሽ አለሙ እና መልካሙ ሰጥዬ የተባሉ የሠራዊት አባላት የወገን ጦር እንዳይጎዳ ሽፋን በመስጠት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አሃዳቸውም አኩሪ ድል እንዲቀዳጅ አድርጓል፡፡ ጠላት አሀዳቸውን በመክበብ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገውን ሙከራ በማክሸፍ ሰብሮ እንዲወጣ በማድረግ አናብስቶቹ በነበራቸው ተጋድሎ የጠላትን ቅስም ሰብረዋል፡፡
በከፍተኛ ቁጭት፣ እልህ እና ወኔ ድጋሚ የጠላትን ምሽግ ሰብሮ በመግባትም ጠላትን ከነጀሌዎቹ ሙትና ቁስለኛ እንዲሁም ምርኮኛ አድርገዋል፡፡ ለዚህም የአዋጊዎች የመሪነት ብቃት እና ጥሩ የመናበብ ውጤት መኾኑን ነው ጀብድ የፈጸሙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት የተናገሩት፡፡
አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል በአጭር ጊዜ በማጽዳት ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የድል ብስራት እና ነጻነት እንደሚያጎናጽፉ ነው የሠራዊት አባላቱ የተናገሩት፡፡ ሀገራችንን ብለን እስከወጣን ድረስ የማንከፍለው መስዋእትነት የለም ያሉት የሠራዊቱ አባላት አሸባሪው በአማራ እና አፋር ክልሎች እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ በመቀልበስ ለሕዝቡ አስተማመኝ ሰላም እንደሚያጎናጽፉም ቃል ገብተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከጋሸና ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ