
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2ዐ12 ጥራትን፣ ተናባቢነትንና ተፈፃሚነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ለዉጡን ሊደግፉ የሚችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን አንደሚሠራ አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ አስታወቁ፡፡
ለፓርላማ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት አሠራራቸውንና አደረጀጀታቸውን ፈትሾ በማስተካከል የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮችን በመፍታት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባም አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዘንድሮው ዓመት በ2ዐ11 ለምክር ቤቱ በዋና ኦዴተር ከቀረበው ሪፖርት ግኝት በመነሳት የተጓደሉ የአሠራር ሥርዓቶችን ፈትሾ በማስተካከልና የሀብት አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት የሀገሪቱ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ አፈ ጉባኤ ተናግረዋል፡፡
በምክር ቤቱ በአምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ የሀገራዊ ምርጫ እና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን፣ በምክር ቤቱ የጸደቁ አዋጆችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተፈፃሚነታቸውን በመከታተል ግልፅና ተዓማኒነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቅም አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በ4ኛ ዓመት የምርጫ ዘመኑ የምክር ቤት አባላት ከወትሮው በተለየ መልኩ በሚወጡ ሕጎች ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ክርክር አንዲሁም ባለተለመደ መልኩ በተቃውሞና በድምፀ ተዓቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ ሕጐች መጽደቃቸውን አፈ ጉባኤው አስታውሰው ይህም በምክር ቤቱ ዴሞክራሲ እየጎለበተ መምጣቱን አመላካች በመሆኑ ዘንድሮም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዋናነት ሕግ የማውጣት ተግባርን የሚያከናውን ሲሆን በ2ዐ11 ዓ.ም የወጡ ሕጎች በሀገሪቱ ከተጀመረው ለውጥ ጋር የሚጣጣምና አጋዥ የሆኑ ሕጐች ጸድቀው ወደ ተግባር መገባቱንም ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በ2ዐ11 ዓ.ም ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ አንዳንድ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመለየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፈታት የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች የመዘርጋትና የመቋቋሚያ አዋጆችንም ጭምር እንዲሻሻሉ የማድረግ ሠራ መሠራቱን አፈ ጉባኤው አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የፌዴራል ዋና ኦዴተር መስሪያ ቤት ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን የፋይናንስና የክዋኔ ሪፖርት ግኝትን መነሻ በማድረግ ለሚመለከተው አካል በተደረገው ሪፖርት በ2ዐ11 በጀት ዓመት ከ1ዐ በላይ የተቋማት ኃላፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ግለፀዋል፡፡
በቀጣይ የምክር ቤቱን አሠራር በማዘመን ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለው መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ከመደበኛ ስብሰባዎች በተጨማሪ የቋሚ ኮሜቴ ስብሰባዎችን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በቀጥታ እንዲተላለፉ በማድረግ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ለማስፈን እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡
በምክር ቤቱ በሚወጡ ሕጎች ኅብረተሰቡን ተሳታፊ ለማድረግ እንደተቻልም ውይይት የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በየደረጃ ለሚገኙ መዋቅሮች ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተሣትፎ ለማጐልበት እንደሚሠራም አፈ ጉባኤው አመልክተዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በምክር ቤቱ የጸደቁ ሕጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በማደራጀት ጠንካራና ደካማ ጐኖችን በመፈተሽ ለቀጣይ ሥራ ግብዓት እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር አንዲውሉ እንደሚሠራም ነው ያመለከቱት፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ማለትም መስከረም 26 ቀን 2012ዓ.ም በይፋ ይከፈታል፡፡
ምንጭ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት