
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “ፍፃሜ መንግሥት” በሚል ስያሜ ከሚጠሩት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ጀምሮ የመጨረሻው የየጁ መስፍን ዳግማዊ ዓሊ ወይም ዓሊ ትንሹ በአይሻል ጦርነት ላይ በደጃች ካሳ ኃይሉ እስከተሸነፉበት 1845 ዓ.ም ድረስ ያለውን ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ “ዘመነ መሳፍንት” ሲል ያስቀምጠዋል፡፡ እንደጉልቻ በየጊዜው የሚለዋወጡት የዘመነ መሳፍንት ነገሥታት ኢትዮጵያን በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር መምራት አቃታቸው፡፡ ሀገሪቱም እንደ አቡጀዲ ለብዙ ነገሥታት እና መሳፍንት ተቆራረሰች፡፡
በዘመነ መሳፍንት በኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ነገሥታት ቢለዋወጡም ሥልጣን አልባ ድኩማን ሆኑ፡፡ መሳፍንቱ ከደረሰባቸው ቅሌት ማገገም ተስኗቸው ተስተዋሉ፡፡ ነገሥታቱ ስልጣናቸውን የሚያፀኑበት እና የሀገር ድንበር የሚያስከብሩበት ሠራዊት አልባ ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያ ሥነ መንግሥትን ለዓለም ሀገራት እንዳላስተማረች ሁሉ በዘመነ መሳፍንት ክፍቷን ውላ ክፍቷን አደረች፡፡
ራስ ወልደ ሥላሴ ከሞቱ በኋላ በእግራቸው ደጃች ሱባጋዲስ የትግሬ የበላይ ገዥ ሆኖ ተተካ፡፡ ለዘመነ መሳፍንት መምጣት አንድ መንስኤ ተደርጎ የሚወሰደውና ወልደ ሥላሴ ከየጁ መሳፍንት ጋር ጀምሮት የነበረውን ፉክክር ደጃች ሱባጋዲስም ቀጥሎበት 1823 ዓ.ም ደብረ ዓባይ ላይ ከራስ ማርየ ጋር ጦር ገጠመ፡፡
ለኢትዮጵያ የመፈራረስ አደጋ እና ለዘመነ መሳፍንት መምጣት ምክንያት የነበሩት እነዚህ የትግራይ ገዥዎች ደጃች ሱባጋዲስ ተሸንፎ እና በራስ ማርየ ጦር ተማርኮ ተገደለ፡፡ የሱባጋዲስ ሞትም የዘመነ መሳፍንት ዘዋሪዎቹ ልሂቃን እና የትግሬ ውድቀት ሆኖ ተመዘገበ፡፡
ዘመነ መሳፍንት ለሀገር አንድነት በጋራ ከመቆም ይልቅ አንዱ ለሌላኛው ፈጽሞ የማይተኛበት ዘመን ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የዘመነ መሳፍንት ሥርዓት አራማጆች ለኢትዮጵያ አንድነት ካስማ እና ማገር ነው ያሉትን ኃይል በግዛት መስፋፋት ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም ለመከፋፈል ጠንካራ ጥረት አድርገው ነበር፡፡
በፖለቲካው መስክ ዘግይቶም ቢሆን እንደታየው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት ለመሸራረፍ እና ብዙ ትንንሽ ግዛት ለማድረግ የተፈጠረውን መሰነጣጠቅ ለማስታረቅ የሞከረው ደጃች ካሳ ኃይሉ (ዳግማዊ ቴዎድሮስ) ነበር፡፡ መሳፍንቱ ለስልጣን ሲራኮቱ የሥርዓቱ ተሸካሚ የሆነው ገበሬ እነዚህን ሁሉ ለመመገብ ይደክም ነበር፡፡
በጎንደር ዙሪያ ይሽከረከር በነበረው የዘመነ መሳፍንት ፖለቲካ ያልተሳተፉ አካላት በወቅቱ ያልተነኩ ቢመስሉም የኋላ ኋላ ግን ጉዳቱ እነርሱንም አገኛቸው፡፡ የዘመነ መሳፍንት ልሂቃን እና የሥርዓቱ ዘዋሪዎች አንዱን መሳፍንት ከአጎራባቹ መሳፍንት ጋር እያናከሱ እርስ በእርሱ እንዳይተባበር ቢያደርጉትም ዳር የቆሙትም መሃል የተገኙትም እኩል የመከራ ገፈት ቀማሾች ሆኑ፡፡ ከምንም በላይ ለሰባት አስርት ዓመታት የዘለቀው የዘመነ መሳፍንት ሥሪት ኢትዮጵያን አቆረቆዛት፡፡
ወቅቱ በዘመነ መሳፍንት ባንዳዎች ከሚሽከረከረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጡዘት በስተጀርባ ሌላ ውጫዊ የግጭቱ አባባሽ ነዳጅ ብቅ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ ምንጊዜም ከኢትዮጵያ የእርስ በርስ ሽኩቻ ጀርባ ተፈልገው የማይጠፉት ግጭት ጠማቂ እና የእብድ አስታራቂ ምዕራባውያን ከ200 ዓመታት በኋላም ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ብቅ አሉ፡፡
በ1625 ዓ.ም አፄ ፋሲለደስ የውጭ ኀይሎችን ከሀገር ካባረሩ በኋላ በኢትዮጵያ እና አውሮጳ መካከል የተበጠሰው እህል ውኃ ዳግም የሚያንሰራራበት በር ተከፈተ፡፡ ለ200 ዓመታት ያክል ኢትዮጵያውያን የፈረንጅ ፊት ዳግም አያሳየን ብለው በራቸውን ዘግተው ይኖሩ ነበር፡፡ በዘመነ መሳፍንት ወቅት ግን በዲፕሎማሲ፣ በንግድ፣ በእምነት እና በምርምር ስም ወደ ኢትዮጵያ የዘለቁት ምዕራባውያን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ዘመነ መሳፍንትን በሴራ አጦዙት፡፡
“ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ አበው የዘመነ መሳፍንት የነገሥታቱ የውስጥ ሽኩቻ የሳባቸው ምዕራባውያንን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሀገራትንም ነበር፡፡ ምዕራባውያኑ ከ200 ዓመታት መራቅ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሁለነገራቸው በዳበሳ ላይ የተመሰረተ እና እምብዛም ለወቅቱ አስጊ አልነበረም፡፡ ነገር ግን እነርሱን እግር በእግር ተከትለው የገቡት ግብፆች የኢትዮጵያ እና የዚያ ወቅት እውነተኛ ስጋት መሆናቸው አልቀረም ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ከግብጽ በላይ ስጋት የፈጠረ ሀገር ኖሮ አያውቅም፡፡ ከ19ኛው መቶ ክፍለዘመን መባቻ ጀምሮ ኢትዮጵያን በብርቱ የተፈታተነቻት ግብጽ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ የግብጽ ፈተና ለመቋቋም ባደረገችው አጸፋዊ እንቅስቃሴ ለዘመናዊ ትንሳኤዋ መንገድ ጠርጋለች፡፡
በዘመነ መሳፍንት የነገሥታቱ ሽኩቻ እና ቅርምት ከስሞ የነበረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለመመለስ፣ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት እና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ለማቋቋም ጊዜው የደረሰ፡፡
የውስጡንም ሆነ የውጭውን አደጋ፣ የሚፋለሙትን መሳፍንትም ሆነ የውጭውን ከበባ በውል ተረድቶ አንድ እና ጠንካራዋን ኢትዮጵያ እንደገና ለመመለስ መንገድ ጠራጊው ደጃች ካሳ ኃይሉ ነበር፡፡ ደጃች ካሳ ኃይሉ በ1847 ዓ.ም “ዳግማዊ ቴዎድሮስ” ተብሎ ዙፋን ሲጨብጥ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ልደት አብሳሪ የተባለውም ለዚህ ነበር፡፡ ካሳ “ቴዎድሮስ” ለመሆን የበቃው በነበሩት የግል ባህሪያቱ እና በጠንካራ ኢትዮጵያዊነቱ ነበር፡፡ ራሱን አንድ ዐቢይ ተልዕኮ ለመፈጸም የታጨ አድርጎ ማየቱ፣ ወታደራዊ ችሎታው፣ ጀግንነቱ እና አዲስ ሐሳብ ተቀባይነቱ የተለየ ነበር፡፡
ራሱን በራሱ ከሽፍትነት ወደ አፄነት ለመቀየር የቻለ ሰው ነበር፡፡ በዘመነ መሳፍንት ተወልዶ የዘመነ መሳፍንት ማርከሻ ፍቱን መድኃኒት የሆነ ጀግና፡፡ ቴዎድሮስ ግን ኢትዮጵያን ከዘመነ መሳፍንት መንጋጋ ለማላቀቅ ከሌላ ፕላኔት አልመጣም፡፡ ትውልድ እና እድገቱ ለኋለኛው ዘመኑ የፖለቲካ ብስለቱ መሰረት ያስያዘው እርሾ እንደነበር የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡
ካሳ ለፍትሕ እና ለእኩልነት የሚቆረቆር ምቾት እና ብልጭልጭ ነገር የማያታልለው የወታደሮቹን ሕይዎት የሚኖር እና የሚጋራ አርአያ የሆነ መሪ ነበር፡፡
የዚህ ዘመን የአባቶቻቸው”የዘመነ መሳፍንት ህልመኞች!” ኢትዮጵያን ዳግም ፈርሳ እና አንሳ እንዲያዩ ከግራ ከቀኝ ሲባክኑ እያየን ነው፡፡ ዘመነ መሳፍንትን ብሔር በሚል ታርጋ እና መለያ ቀይረው ብቅ ያሉት የሽብርተኛው ትህነግ ገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች እንደ ቀደምት ባንዳ አባቶቻቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ የነቃ ትውልድ ላይ ደርሰው ሕልማቸው ከሸፈ እንጂ፡፡
የሽብርተኛው እና ወራሪው ትግራይ ኃይል አነሳሱ እና ሕልሙ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ታላቋን ትግራይ መገንባት ቢሆንም ከሕዝብ በመጣ ወጀብ እና ማዕበል ምኞታቸው ሳይሳካ ወደ ናፈቁት ሲኦል እየወረዱ ነው፡፡
ርዝራዦቻቸው ዛሬም እንደ ትናንቱ በአማራ ሕዝብ ደም ተረማምደው የኢትዮጵያን መፍረስ ሊያውጁ ቢያስቡም ዳግም ይህንን እድል የሚሠጣቸው ትውልድ አልተገኘም፡፡ እርግጥ ነው በሕይዎት እና በሞት መካከል ሳሉ ለትግራይ ሕዝብ ሕልውና በሚል የተሰጣቸው የጥሞና ጊዜ ለአማራ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ ሕልውና ስጋት ቢሆንም ዋጋ ይከፈል ይሆናል እንጂ ይህ ትውልድ እያለ ኢትዮጵያን ለባንዳ ልጆች የሚሰጥ የዋህ ሕዝብ አይኖርም፡፡
ይህ ትውልድ ቴዎድሮስ ምሳሌው እንጂ ፍፃሜው አይሆንም፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት እንደቆመች፣ ባሉት እንደጸናች በሚመጡትም ትቀጥላለች፡፡ ከክፉዋ አፋፍ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ዳግም በሀገራቸው ጉዳይ ፈጽመው ስህተት በማይሠሩ እና በማይደራደሩ ልጆቿ ከፈተናዎቿ እየተሻገረች አዲስ ሆና ትታያለች፡፡ መፈተን መውደቅ አይደለም፤ መፈተን መውደቅ ቢሆን እንደ ኢትዮጵያ ማን የተፈተነ ነበር፡፡ ይህ ትውልድም እንደ አባቶቹ ከትቶ፣ መክቶ እና አንክቶ ሀገሩን የዘመነ መሳፍንት ህልመኞችን ቀቢጸ ተስፋ አምክኖ፣ የውጭ ኀይሎችን ሴራ አክሽፎ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ተጨማሪ ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ (በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ)
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ