❝ራሳችንን ነፃ ለማውጣት፣ ክብራችንና ታሪካችንን ለመጠበቅ የምንሰስተው ሕይወት አይኖርም❞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን

54
ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ኃይል ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ንጹሐንን በግፍ ገድሏል፣ ሀብትና ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟል፤ ይህንን እኩይ ድርጊቱን አሁንም ቀጥሎበታል።
አሸባሪውና ወራሪውን የትግራይ ኃይል ለማጥፋት መላው የአማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ እየታገለው ነው። አሸባሪ ኃይሉን ወረራ ለመቅበር የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ፣ ሚሊሻና ሕዝቡ ያልተቋረጠ ተጋድሎ እያደረጉ ነው።
ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር እየተደረገ ስላለው ተጋድሎ ለአሚኮ ሐሳባቸውን የሠጡት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳደሪ አብዱ ሁሴን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በወሎ ምድር ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ወገኖችን እየገደለ፣ ንብረት እየዘረፈ፣ ተቋማትን እያወደመ፣ የአርሶ አደሩን ሰብል እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪውና ወራሪውን የትግራይ ኃይል አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ራሱን አደራጅቶ ትግል መጀመሩንም አስታውቀዋል። የዞኑ አስተዳደር በየወረዳው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ በማሰማራት ጠላትን ለመደምሰስ እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
መላው አማራ የጀግኖች አባቶች ልጅ መሆኑን የሚያሳይበት፣ ወራሪውና ዘራፊውን የትግራይ ኃይል ከወረራቸው አካባቢዎች ነቅሎ ለመጣልና በሌላ ጊዜም ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል። ይህም በቅርብ ቀን ውጤት እንደሚያስመዘግብም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ከሌሎች ዞኖች የተውጣጡ ኃይሎችም በዞኑ መሠማራታቸውንም ተናግረዋል።
ጠላትን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ሁሉም አካል ሀብትና ንብረቱን ከዚያም አልፎ እስከ ሕይወት መስዋእትነት የሚደርስ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለንም ነው ያሉት።
❝ለዚህ ትግል መቆጠብ ያለበት ሀብት የለም፤ ራሳችንን ነፃ ለማውጣት፣ ክብራችንና ታሪካችንን ለመጠበቅ የምንሰስተው ሕይወትም አይኖርምም❞ ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ባስተላለፈው የክተት ጥሪ መሠረት ሁሉም የሰው ኃይል፣ ሀብትና ንብረት ወደ ግንባር መሆን አለበት ነው ያሉት።
ጠላት እየተጠቀመ ያለው ስልት በአሉባልታ መበተን፣ መሪ እንዳይኖር ማድረግ፣ በውስጥ ገብቶ መሸርሽር ነው ያሉት አቶ አብዱ የጠላትን እንቅስቃሴዎች ማምከን ከቻልንና መተባበር ከቻልን ጠላትን መደምሰስ እንችላለን ብለዋል።
መደማመጥ፣ መተባበር እና ትክክለኛ መረጃዎችን ከትክክለኛው ምንጭ በመውሰድ በዚያ ላይ የተመሰረተ ትንተና መሥጠት እንደሚገባም ጠይቀዋል።
የማኅበራዊ አንቂዎችና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የጠላትን ዓላማና የግፍ ሥራ በማጋለጥ ሕዝቡ ጠላት ላይ ያለው እይታ እንዳይከፋፈል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ሕዝቡ በጠላት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል። አሁን ላይ ጠላትን ለመቅበር የሚያስችል የሕዝብ ንቅናቄ መፈጠሩንም አንስተዋል።
ሕዝቡ በአሉባልታ ሳይረበሽ አካባቢውን ሳይለቅ ባለበት ሆኖ ጠላትን እንዲታገልም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠላት ተወረሃል እያለ በፕሮፖጋንዳ እንደሚያወናብድ፣ በተላላኪዎቹም ሽብር ስለሚነዛ ይህንን በውል በመረዳት ትግል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የልማት ሥራም ሆነ ጦርነት ውጤታማ የሚሆነው መሪ ከፊት ሲሆን ነው ያሉት አስተዳዳሪው ጦርነት ከፊት ሆኜ የምመራው ለሕዝብና ለራሴም ክብር ነው ብለዋል።
❝በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተገዝቶ መኖር የሚያስችል ስብዕናም ማንነትም ማንኛውም አማራ ሊኖረው አይገባም❞ ነው ያሉት።
የዞኑ መሪዎች ጠላትን መፋለም የሚያስችል ስምሪት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል።
ለህልውና ዘመቻው በሀገር ውስጥ ኾነ በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
❝የራሳችንን ነፃነት በራሳችን መስዋእትነት እናስከብራለን፤ ሕዝቡ እንደተለመደው ሠራዊቱን በሞራል፣ በገንዘብና በመረጃ የመደገፍ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል❞ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሴቶች እየተደፈሩ እና እናት አባቶቻችን እየተገደሉ ማንንም ቆሜ ላስተምር አልችልም” መምህርት ምዕራፍ ፍቃዴ
Next article❝ራሳችንን ነፃ ለማውጣት፣ ክብራችንና ታሪካችንን ለመጠበቅ የምንሰስተው ሕይወት አይኖርም❞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን