
ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪና ዘራፊ ኃይል በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ ፈፅሟል። ወረራ በፈፀምባቸው አካባቢዎችም ዜጎችን በግፍ ገድሏል፣ ሀብትና ንብረታቸውን አውድሟል፣ ከቤትና ንብረታቸው አፈናቅሏል። የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከቻለም ለማፍረስ መውተርተር ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም የሽብር ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ላይ ነቅሎ ለመጣል ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
መንግሥት ሀገርን ለመታደግ ሁሉም ለሕልውና ዘመቻው አበርክቶ እንዲኖረው ጥሪ አቅርቧል። በቀረበው ጥሪ መሠረትም ኢትዮጵያውያን አሸባሪና ዘራፊው የትግራይ ኃይል በግንባር ለመፋለም እየተመሙ ነው። በአማራ ክልል ትኩረቶች ሁሉ ወደ ሕልውና ዘመቻው እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
የሕልውና ዘመቻውን በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመካነ ሰላም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተስፋዬ ዳኘ ከተማ አስተዳደሩ ለሕልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ዝግጅት አድርጎ ትግበራ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
አሸባሪው የትግራይ ኃይል የአማራ ክልልን መውረር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወረራውን ለመቀልበስ በልዩ ትኩረት ሲሠሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ያሉት ከንቲባው ድል ለማምጣት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አስቀድመው መሥራታቸውን ነው የገለፁት። በከተማ አስተዳደሩ ለሕልውና ዘመቻው በግንባር የሚሳተፉ ታጣቂዎች መዘጋጃታቸውንም ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ወደ ትግል ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። የሎጅስቲክ አቅርቦት በማሟላት በኩልም ከኅብረተሰቡ ጋር መሥራታቸውን ተናግረዋል። ለሠራዊቱ አስተማማኝ ደጀን ለመሆን የሚያስችል ሥራ እየሠሩ ስለመሆናቸውም ገልፀዋል።
በከተማዋ ሰርጎ ገብ እንዳይኖር ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች እና የታጠቀው ኃይል ዝግጅቱን አጠናቅቋል ነው ያሉት።
ጠላት ሀገርን ለመበተን እየሠራ ነው፤ ይሄን የማይመክትና ከፊት ሆኖ የማይመራ መሪ በከተማችን የለንምም ብለዋል።
በመሪዎቹ በኩል የቁርጠኝነት ችግር አለመኖሩንም ገልፀዋል። በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመንከባከብ ከተማ አስተዳደሩ በተቻለው ሁሉ እየሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። የከተማዋ ሕዝብም በከፍተኛ ሁኔታ እያገዛቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት ተፈናቃዮችን በመደገፍ በኩል በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል። በከተማዋ ተፈናቅለው ያሉ ወጣቶችን የትግሉ አካል ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ለሕልውና የተዘጋጁ የቦረና ወረዳና የመካነ ሰላም ነዋሪዎችም በሕልውና ዘመቻው ያልተሳተፈውን ከወራሪው ለይተን አናየውም ነው ያሉት። ሀገር ስትደፈር ቆመን አናይም፣ የአማራ ምድር ለወራሪውና አሸባሪው ኃይል መቀበሪያ እንጂ መፈንጫ አይሆንምም ብለዋል።
ሁሉም ሰው ወደ ሕልውና ዘመቻው እንዲተምና በአጭር ጊዜ ሀገርና ሕዝብን ነጻ መውጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ