“ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ደጃችን እስኪደርስ አንጠብቅም፤ ካለበት ሄደን እናጠፋዋለን” የሰሜን ጎንደር ዞን ዘማቾች

112
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ የተቀበሉና ሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ የሰሜን ጎንደር የሥራ ኀላፊዎችና ዘማቾች በኅብረተሰቡ፣ በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ወደ ግንባር ተሸኝተዋል፡፡
ዘማቾቹ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሕዝቡ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋና ዘረፋ እየፈፀመ የሚገኘውን ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል እስከ መጨረሻው ለማጥፋት ቆርጠው መነሳታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በደባርቅና ዳባት ወረዳ የጀግንነት ተጋድሎ ማድረጋቸውን ዘማቾቹ ጠቅሰዋል፡፡ “በደባርቅና ዳባት ወረዳ የተዋጋነው ከተማችንን ከዝርፊያ፣ ሕዝባችንን ከጅምላ ጭፍጨፋ ለመታደግ ነበር፤ አሁን እየዘመትን ያለነው ግን ጠላትን እስከመጨረሻው አጥፍተን ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ነው” ብለዋል፡፡
ዘማቾቹ በቁጭት እንደተናገሩት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች በርካቶችን በጅምላ ጨፍጭፏል፡፡ “ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ደጃችን እስኪደርስ አንጠብቅም፤ ካለበት ሄደን እናጠፋዋለን” ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ባስተላለፈው የክተት ጥሪ መሠረት የደባርቅ ከተማ የሥራ ኀላፊዎችም ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ለማጥፋት የደባርቅ፣ የዳባት እና የአካባቢውን ዘማቾች እየመሩ ወደ ግንባር ዘምተዋል፡፡
ከሥራ ኀላፊዎች መካከል የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መብራቱ ሙሉጌታ ሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ለማጥፋት እርሳቸውን ጨምሮ የሥራ ኀላፊዎች ግንባር ቀደም ሆነው የፀጥታ ኃይሉን፣ ታጣቂውንና ወጣቱን በመምራት ወደ ግንባር እየዘመቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ መብራቱ ከዘማቾች ባለፈ ከተማውንና አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች እና ተላላኪዎች የሚጠብቅ የተደራጀ ኃይል መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የደባርቅ ከተማና አካባቢው ማኅበረሰብ እንዳሁን ቀደሙ ሁሉ እንቅልፍ ለምኔ ብሎ ለሠራዊቱና ለዘማቾች ስንቅ በማዘጋጀትና ደጀን በመሆን፣ አካባቢውን ከሰርጎ ገብ በመጠበቅ፣ ለሀሰት ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ባለመስጠት የህልውና ዘመቻውን በማገዝ የድሉ ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሕልውና ዘመቻው የንግዱ ማኅበረሰብ ከምንግዜውም በላይ ግብሩን በአግባቡ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የገቢዎች ቢሮ አሳሰበ።
Next articleበሕልውና ዘመቻው ያልተሳተፈውን ከወራሪው ለይተን አናየውም❞ የቦረና ወረዳና የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች