
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ጸጋ ጥበቡ (ዶክተር) በሰጡት ማብራሪያ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር አድርጓል። ከዚህም ውስጥ አንዱ አማራ ክልል በመንገድ፣ መብራት፣ ውኃ እና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲጎዳ ሲያደርግ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ወራሪው እና አሸባሪው ኀይል ዛሬም ከውጭና ከሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር አከባቢዎች ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ አካሂዷል፣ የቻለውን ሀብትና ንብረት ዘርፎ ያልቻለውን ከጥቅም ውጭ በማድረግ የክልሉ ሕዝብ በድህነት እንዲኖር የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በውጭም ኾነ በሀገር ውስጥ እየፈጠረ ያለውን የኢኮኖሚ አሻጥር ለማሸነፍ የንግዱ ማኅበረሰብ ግብሩን በአግባቡ መክፈል እንዳለበት አሳሰበዋል፡፡
አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ አውደ ውጊያዎችን የከፈተውን ወራሪና አሸባሪ ኀይል ለማጥፋት እየተካሄደ ባለው የሕልውና ዘመቻ የንግዱ ማኅበረሰብ ከምንግዜውም በላይ ግብሩን በአግባቡ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ዶክተር ፀጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብ ግብርን በወቅቱ ከመክፈል ባሻገር በሕልውና ዘመቻው ልዩ ልዩ ድጋፎችን እስከ ሕይወት መስዋእትነት እየከፈሉ ያሉ የመኖራቸውን ያክል ለተገልጋዮች ደረሰኝ ባለመስጠት እና በሕገ ወጥ ንግድ በመሳተፍ የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድም ቢሮ ኀላፊው አሳስበዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ከሕልውና ዘመቻው ጎን ለጎን ግብር ለመሰወር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምየ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ