
በአማራ ክልል መንግሥት የተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ ጥሪውን ተከትሎ በረድኤት ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ማኅበራት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት የአፈፃፀም መመሪያ አወጣ።
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ገረመው ገብረጻዲቅ የመንግሥት ተቋማት እና የረድኤት ድርጅቶችን አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ጥቅምት 21/2014 ዓ.ም ባካሄደው አሥቸኳይ ስብሰባ ክልሉ በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የተደቀነበትን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችሉ ዘጠኝ ነጥቦች ያሉት የአስቸኳይ ጥሪ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መውጣቱንም ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በምክር ቤቱ ከወጡ አስቸኳይ ውሳኔዎች መካከል ደግሞ አገልግሎታቸው በከፊልም ኾነ ሙሉ በሙሉ የሚቋረጡ እና የማይቋረጡ ተቋማት ይገኙበታል፡፡
በዘመቻ መምሪያው እየተለዩ አገልግሎታቸው እንዲቀጥል እና አገልግሎታቸው በሙሉም ኾነ በከፊል እንዲቋረጥ የሚደረጉ ተቋማት እንዳሉ ኾኖ በግብርና እና በመስኖ ልማት የተሰማሩ ተቋማት እና ዘርፉን የሚመሩ የሥራ ክፍሎች፣ ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት፣ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ተቋማት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የጸጥታ ተቋማት፣ በፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ እና ድጋፍ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተግባራቸው እንደማይቋረጥ ነው ያብራሩት፡፡
አቃቤ ሕግ እና ፍርድ ቤቶች ከሕልውና ዘመቻው ጋር የተለዩ የወንጀል አይነቶች እና ጊዜ የማይሰጡ ክርክሮችን በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እና በፍትሕ ቢሮ የበላይ ኀላፊዎች አማካኝነት ተለይተው አገልግሎታቸውን በከፊል እንደሚቀጥሉም ኀላፊው አንስተዋል፡፡
በክልሉ መንግሥት የተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ ጥሪውን ተከትሎ በረድኤት ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ማኅበራት ፋይናንስ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የአፈፃፀም መመሪያ መውጣቱም ተገልጿል። ይኹን እንጅ እነዚህ ተቋማት በሀብት ማሰባሰብ፣ ተሸርካሪ በመተባበር የህልውና ዘመቻውን ለመደገፍ ፈቃደኛ ከኾኑ እንደሚበረታቱ ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ የሕልውና ዘመቻውን የሚያደናቅፉ ማንኛውም ተግባር ፈጽመው ከተገኙ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ኾነ በክልሉ በወጣው መመሪያ ርምጃው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አንስተዋል፡፡
በየተቋማቱ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችም ዘማቾችን በመመልመል፣ ሃብት በማሰባሰብ፣ የአካባቢውን ደኅንነት መጠበቅ እና ግንባር እስከ መሰለፍ ኀላፊነት እንዳለባቸው በአስቸኳይ ጥሪ ውሳኔው መቀመጡን አቶ ገረመው ገልጸዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል አገልግሎታቸው የተቋረጡ ተቋማት የመንግሥት ሠራተኞችም ከቤታቸው ይቀመጣሉ ማለት ሳይኾን በሥራ ሰዓት ከሥራ ቦታቸው በመገኘት እንደ ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዘመቻውን በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፉ ነው የተናገሩት፡፡
የሚያከናውኗቸው ተግባራትም የስንቅ እና የትጥቅ ዝግጅት፣ በዘመቻው መሳተፍ የሚፈልግ መዝመትና ሌሎች ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ነው ያስረዱት፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ