
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በአማራ እና በአፋር ክልል እየፈጸመ ያለውን ግፍ ለማስቆም የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይልን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ነዋሪ ተፈሪ አገሬ የራሱን እና የቤተሰቡን ኑሮ በባጃጅ ሹፌርነት ተቀጥሮ በሚያገኘው ገቢ ነው የሚመራው፡፡ ተፈሪ እንዳለው “ሀገር ለማዳን የሌላን አካል ድጋፍ መጠበቅ አያስፈልግም፤ ራሳችንን መታደግ የምንችለው ራሳችን ነን” ብሏል።
“ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ካለንበት ድረስ መጥቶ እንዲገድለን መጠበቅ የለብንም፤ ካለበት ቦታ ድረስ ሄደን እንፋለማለን፤ ቁጭ ብለን ሞትን እና መፈናቀልን አንጠብቅም” ነው ያለው፡፡
ለጠላት ጊዜ መስጠት አይገባም ያለው ተፈሪ ጠላትን በጋራ በማጥፋት ለልማት ለመሠለፍ ጊዜው አሁን ነው ብሎናል፡፡ የቤተሰቦቼ ሕይወት በኔ ሥራ ላይ የሚወሰን ቢሆንም ከሀገር የሚበልጥ ነገር ስለሌለ የጸጥታ ኃይሉን ተቀላቅያለሁ ብሏል።
ወጣቱ ሀገሩን የእናት ጡት ነካሽ ለሆነው የትግራይ ወራሪ ኀይል አሳልፎ ላለመስጠት በቁርጠኝነት ሊሰለፍ እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ሁሉም ወጣት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም ጠይቋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት መላኩ በለጠ በግል ሥራ የተሠማራ ነው፡፡ ወጣት መላኩ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ለማስቆም ልዩ ኀይልን መቀላቀሉን ገልጿል።
ወጣት መላኩ እንዳለው ካጋጠመን የህልውና አደጋ ለመውጣት ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በመተሳሰብ መሠለፍ ይጠበቅብናል ብሎናል፡፡
“በአባቶቻችን ደም እና አጥንት ተከብራ የኖረችን ሀገር በእኛ ጊዜ በእኛ እድሜ ማስደፈር የሞት ሞት ነው፤ ወጣቱ ሊነሳ ይገባል፤ በተለያዩ አደረጃጀቶች መሳተፍ አለብን፤ ለሀገራችን እኛ ልጆቿ እያለን ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ኢትዮጵያን አያፈርስም” ብሏል፡፡
ወጣቶች ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር አሸባሪ ኃይሉ አማራን ከማጥፋት እንደማይመለስ ማወቅ አለባቸው ነው ያለው።
“ወጣቶች ልንነቃ ይገባል እኔ እና ጓደኞቼ የጸጥታ ኃይሉን ተቀላቅለናል፤ ሌሎቻችሁም እድሉን ተጠቀሙበት‟ ሲል መክሯል፡፡
ዘገቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ