“አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይልን በከፍተኛ ሕዝባዊ ማዕበል እየደመሰስነው ነው” የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪዎች

106
ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬም እንደ ትናንቱ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን በጠላት የተለመደውን ጀብድ እየፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የዋግ ሕዝብን ያልፈጸመበት የበደል አይነት የለም የሚሉት ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነውን የሽብር ኀይል ዛሬም እንደትናንቱ በከፍተኛ ወኔ ተነስተው እየተፋለሙት እንደሆነ ነው የሚገልጹት።
የአበርገሌ፣ የፃግብጂ፣ የዳህና፣ የሳህላ ሰየምት፣ የዝቋላ፣ የሰቆጣ እና የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች በየአቅጣጫው እየተመመ ከሚገኘው ወገን ጋር በመሆን አሸባሪውን ኀይል እየቀጡት ነው። ስንቅ ይዘው መምጣታቸውን የገለጹት ነዋሪዎች ሕዝቡ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ከቀጠለ ጠላትን በቀላሉ መደምሰስ እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይል በአሁኑ ወቅት በከበባ ውስጥ ገብቷል፤ ምርጫው እጅ መስጠት ወይም ባለበት ማለቅ ሊሆን እንደሚችል ነው ያብራሩት።
የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አብራው ዘገየ አሸባሪ ኀይሉ በወረዳቸው ተዘርዝሮ የማያልቅ ሰቆቃ ፈጽሟል ብሏል።
አሸባሪው ኃይል ተጽዕኖ ፈጣሪ የሀገር ባለውለታ ሰዎችን በመግደል፣ ወላድ እናቶች የሚገለገሉባቸውን አምቡላንሶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የግብርና ተቋማትንና መሰል መሠረተ ልማቶችን መዝረፉንና ማቃጠሉን ገልጸዋል። ሕዝቡም ጠላቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ ከፍተኛ ፍልሚያ እያደረገ ነው፤ አበረታች ድልም እየተመዘገበ ነው ሲሉ አሁናዊ ሁኔታውን አስረድተዋል።
አቶ ሃላዩ መኮንን በበኩላቸው አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይል በእናቶችና በሕጻናት ላይ ከአደረሰው ጭፍጨፋ በተጨማሪ ተቋማትን ሲጠብቁ የነበሩ የጥበቃ ሠራተኞችን በመግደል ዘርፏል፤ ያልወሰደውን አቃጥሎ ሂዷል ብለዋል። አሁንም ወራሪው ኀይል በቀያቸው ያሻውን እየፈጸመ መኖር ስሌለበት የመጨረሻ እስትንፋሱን ለመዝጋት በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ሕዝቡ በከፍተኛ ቁጣ ባገኘው መሣሪያ ሁሉ አንድም እንዳይተርፍ አድርጎ እየደመሰሳቸው ነው ሲሉ በዓይናቸው ያዩትን ነግረውናል።
የአበርገሌ ወረዳ የሰላም እና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሸጌ መንግሥቴ እንደገለጹት ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን የሽብር ኃይል ሕዝቡ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ከጸጥታ ኀይል ጋር በመሆን ፍልሚያ እያደረገ ነው። እየተደረገ ያለው ፍልሚያም በከባድ ችግር ውስጥ የወደቀውን ማኅበረሰብ ከሰቆቃ የሚያወጣ ነው ብለዋል። ትግሉም ወራሪው ኀይል የደኅንነት ስጋት መሆን በማይችልበት ደረጃ ማድረስ እንጂ የወረረውን ቦታ ለቆ እንዲወጣ ማድረግ ብቻ አለመሆኑን አረጋግጠዋል።
በሚደረገው ፍልሚያም በርካታ ተተኳሽ ጥይቶችን፣ ክላሽን፣ ስናይፐር፣ ሌሎች መሳሪያዎች መያዝ ተችሏል፤ ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህ ታሪካዊ ትግል መዝመት የሚችል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመዝመት ኢትዮጵያ ዛሬም ለጠላት የማትነካ ገናና ሀገር መሆኗን ለዓለም ልናሳይ ይገባናል፤ ጠላት ከእንግዲህ በኋላ የማሸነፍ ኀይሉ ተዳክሟል ነው ያሉት።
Previous articleለቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ጥሪ ቀረበ።
Next article“ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይል ካለንበት ድረስ መጥቶ እንዲገድለን መጠበቅ የለብንም፤ ካለበት ቦታ ድረስ ሄደን እንፋለማለን” አማራ ልዩ ኀይልን ለመቀላቀል የተመዘገቡ ወጣቶች