
“ሁሉም ጨርቄን ማቄን ሳይል መዝመት አለበት” የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሲሳይ ምስጋናው
ጎንደር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሻባሪውና ወራሪው የትግራይ ኀይል በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍ የተመለከተ ጥናት አካሂዷል። ጥናቱን ካካሄዱት አንዱ መምህር ሲሳይ ምስጋናው (ዶክተር) አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል በአማራ ሕዝብ ላይ ግፍ መፈጸም የጀመረው ከርእዮተ ዓለሙ ጀምሮ መኾኑን ተናግረዋል። አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ የቀኝ ገዢዎችን አስተሳሰብ ለመተግበር በርእዮተ ዓለሙ ማካተቱን ገልጸዋል።
አሸባሪው ኀይል በሥልጣን በነበረበት ወቅትና ከሥልጣኑ ከተወገደ በኋላም በአማራ ሕዝብ ላይ በታሪክ የማይረሳ የተለያዩ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል ነው ያሉት።
አሸባሪው ኀይል የፈለገውን መሬት ለመውሰድና ሀገሪቱን ለመበዝበዝ አልሞ ሲነሳ የመጀመሪያ እንቅፋት ይኾንብኛል ብሎ ያሰበው አማራን ስለኾነ፣ ሥልጣን በያዘበት ወቅት አማራን ሲገድል፣ ሲያሳድድ፣ ሲያፈናቅልና ሲያንገላታ መቆየቱን አስረድተዋል። ይህን የአማራ ጥላቻ ርእዮተ ዓለሙን ለማሳካት አሸባሪው ትህነግ ከደደቢት በረሀ ምስረታው በኋላም በ1978 ዓ.ም ከምእራባውያን ሀገራት የመሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት በሚያስችለው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን አካባቢ ትግል መጀመሩን ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል።
አሸባሪው ኀይል በ1983 ዓ.ም ወደ ሥልጣን ሲመጣ ታላቋን ትግራይ ለማቋቋም ተግዳሮት ይኾኑብኛል ያላቸውን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ታሪክ አዋቂ የኾኑትን ታላላቅ ሰዎች “መሥፍን፣ ባላባት” እያለ ምክንያት እየፈጠረ ማጥፋቱን በጥናታቸው አሳይተዋል። በወቅቱ የአማራ ታሪክ አዋቂዎችን የማፈን ተግባር የቀጠለው ትህነግ እንደ ግህንምና ባዶ ስድስት የተባሉ ማፈኛና መግደያ ቦታዎችን ሲጠቀም እንደነበረ በጥናታቸው አጋልጠዋል።
በርካታ የአማራ ተወላጆች የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን እንዳረጋገጡም ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል። “ግህንም በተባለ ማሰቃያ ቦታ ላይ የአማራን ታሪክ ያውቃሉ የተባሉ 59 ሺህ ሰዎች መጥፋታቸውን በጥናታችን አረጋግጠናል” ብለዋል። አሸባሪው ትህነግ በኀይል በያዛቸው የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች በቋንቋቸው እንዳይናገሩ፣ እንዳይማሩ፣ በባሕላቸው እንዳይኮሩ፣ ማንነታቸውን እንዳያውቁ አፈና ሲፈጽም መቆየቱን ምሁሩ በጥናታቸው አረጋግጠዋል።
አሸባሪው ትህነግ በርእዮተዓለሙ አማራ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጠላ ሲሠራ መቆየቱንም አብራርተዋል።
ከሀዲው ትህነግ በ2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ቅራቅርና ሶሮቃ ላይ ጦርነት ከፍቶ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሲሳይ ትህነግ ለአማራ ያለውን ግልጽ ጥላቻ በማይካድራ ጭፍጨፋ ማረጋገጡን አስገንዝበዋል። አሸባሪው ኀይል ለማይካድራ ጭፍጨፋ ገዳይ ወጣቶችን ሲያሰለጥን እንደቆየና ይህንንም መፈጸሙን በተደረገው ጥናት መረጋገጡን አመላክተዋል።
“በማይካድራ ጭፍጨፋ 1 ሺህ 563 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል 1 ሺህ 534 ሰዎች ደግሞ ቤተሰብ አልባ ኾነዋል። ማይካድራ የአማራ ሕዝብ ሰቆቃ ማሳያ ነው” ብለዋል።
አሸባሪው ኀይል አሁንም “በአማራ ሕዝብ ሒሳብ አወራርዳለሁ” በማለት በተለያዩ አካባቢዎች ወረራ በመፈጸም ዜጎችን እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ ሴቶችን እየደፈረ፣ ሀብት ንብረት እያወደመና እየዘረፈ መኾኑ ለመቶ ዓመት የነበረው ህልም ያከሸፈብኝ አማራ ነው በማለት በርካታ ግፎችን ፈጽሟል፣ እየፈጸመም ይገኛል ብለዋል።
• ዶክተር ሲሳይ አሸባሪውን ኀይል ለማስወገድ መፍትሔ ናቸው ያሉትን ነጥቦችም አስቀምጠዋል።
• ሁሉም ጨርቄን ማቄን ሳይል መዝመት አለበት።
•
• አማራ መደማመጥ፣ አንድ መኾን፣ ልዩነቶችን መተውና ለህልውናው ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል፣ ግዴታውም ነው ብለዋል።
• የተማረው ማኅበረሰብ በዕውቀቱ ለትግሉ ስኬታማነት ማገዝ ይኖርበታል፡፡
• የንግዱ ማኅበረሰብና ባለሀብቱ ነገ ጠላት በሚፈጽመው ወረራ ሕይወቱን፣ ሀብት ንብረቱን ከማጣቱ በፊት ለትግሉ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
• ሕዝባዊ ሠራዊቱ አሸባሪውን ኀይል በግንባር ከመፋለም ባለፈ በስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ