
ደብረታቦር፡ ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ ሠሪው የደቡብ ጎንደር ሕዝባዊ ሠራዊት የቀረበለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር ከትቷል፡፡ የአማራ ሕዝብ የመኖር ሕልውና አደጋ ላይ ወድቋልና ለቀረበለት የክተት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል። ሕዝባዊ ሠራዊቱ የአማራ ሕዝብን አዋርዶ፣ ዘርፎና ገድሎ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተነሳውን አሸባሪ የትግራይ ወራሪ ኀይል ሳያጠፋ ወደ ቤቱ ላይመለስም ተማምሏል።
ማንነቱን፣ ባሕሉን፣ ሀገሩን እና ክብሩን ዳግም ለባንዳ አሳልፎ ላይሰጥ ቃል ገብቶ ወደ ግንባር ያቀናው ኀይልም ሽኝት ተደርጎለታል።
በመርኃግብሩ የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ የሕልውና ዘመቻው የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እስከመጨረሻ ነጻ ለማውጣት እንደሆነ አብራርተዋል። አቶ ሲሳይ እንዳሉት ጠላትን ማጥፋት የዘመቻው መዳረሻ ነው። በሁሉም ግንባሮች ጠላት ዳግም በማያንሰራራበት ደረጃ ለመምታት ዝግጅት መደረጉን በመግለጽም መንግሥት ለዘማቾች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ቀለመወርቅ ምህረቴ ያለመደፈር እልሃችንን በተግባር አሳይተን በምንከትበው የድል ታሪክ ለልጆቻችን ነጻነትን እና ኩራትን እናጎናጽፋለን ብለዋል። “ሕልውናችን የሚረጋገጠው በእያንዳንዳችን ክንድ ጠላትን ደቁሰን ስንመለስ ነው” በማለት የነፋስ መውጫ ጀግኖች በባዶ እጃቸው ከጠላት ጋር ተናንቀው ጀብድ መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።
ዘማቾች ታሪክ እየሠሩ ካሉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ የፋኖ፣ የሚሊሻ አባላት እና የአማራ ሕዝብ ጋር ተሰልፈው ተልዕኳቸውን በጀግንነት እንዲወጡም አስግንዝበዋል።
ሀገርን እና የአማራን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በጽናት መዋጋትና ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ ናቸው። የደቡብ ጎንደር ሕዝብ ሽንፈትን የማይቀበል፣ ባርነትን አጥብቆ የሚጠላ እና በአሸናፊነት የሚዋጋ አኩሪ ታሪክ ያለው የአባቶቹ ልጅ እንደኾነ ተናግረዋል።
የሁሉም ወረዳ የፖለቲካ መሪዎች፣ ሚሊሻዎች፣ የፖሊስ አባላት እና ልምድ ያላቸው ምልስ የሠራዊት አባላት የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል። የሚሰጡ መመሪያዎችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ- ከነፋስ
መውጫ ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ