
ኢትዮጵያ የማዳን ጥሪን ተከትሎ እየተመመ ያለው የሕዝብ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ተጋድሎ የጥፋት ኃይሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ያላትን ዝግጁነትና ተግባር የሚያመለክት ነው፡፡ በቅርቡ በፌደራልና የክልል መንግሥት አስፈፃሚዎች የግንኙነት መድረክ ለመላው ኢትዮጵያውን ለቀረበው ጥሪ መላው ሕዝባችን በተለይም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ያሳየው ምላሽና ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ኢትዮጵያውያን ተቆጥተው በሁሉም አቅጣጫ በተደራጀ አግባብ ወደ ጦር ግንባር እየተመሙ ይገኛሉ፡፡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በማሸነፍ ወኔ፣ ሥነ-ልቦና፣ ጀግነትና ቁጭት ግንባሩን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
የበረሃ አንበሶቹ የአፋር ልዩ ኃይልና አይበገሬዎቹ የአፋር ወጣቶች ወደ ክልላቸው ለመስፋፋት ያሰፈሰፈውን ኃይል ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጋር ኅብር ፈጥረው ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ሽንፈት እንዲከናነቡ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በጠላት ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ጉዳይ አስፈፃሚ አድርጎ ያስቀመጣቸው አመራሮች ላይ ሕዝቡ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በሁሉም ግንባሮች ጠላትን ለመቅበር ሕዝቡና የወገን ጦር አንድነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የአሸባሪው ቡድን ትሕነግና ፍልፍሎቹ አለን የሚሉትን ኃይል በማሰበሰብ በወገን ጥምር ጦር ከበባ ውስጥ እየገቡ ናቸው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎና በወገን ኃይል ከፍተኛ ንቃትና መነሳሳት ተፈጥሯል፡፡ አይጥ ከጉድጓዳ እየራቀች በሄደች ቁጥር መሞቻዋ ነው እንደሚባለው የጠላት ግብዓተ መሬት ተቃርቧል፡፡
የጥፋት ኃይሉ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት የዘር ማጥፋት በትግራይ ሕዝብ ላይ ተፈፅሟል፣ የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ ረሀብ እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል፣ አስገድዶ መድፈርን የትግራይን ሕዝብ ለመቅጫነት የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠቅሟል፣ እና ወዘተ እያለ ሲጠቀምባቸው የነበሩ አሰልቺ ስብከቶቹ በዓለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋም በተደረገው የእውነት ማፈላለግ ሥራ እነዚህ ጉዳዮች በኢትዮጵያ መንግሥት እንዳልተፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡
በቁጣ የተነሳሳው የሕዝብ ማዕበል ያስበረገገው የሽብር ቡድኑ ማሽኖችና በሽርክና የሚሠሩ ሚዲያዎች የመጨረሻ ያሉትን የሽብር ወሬ በማሰራጨት ተጠምደዋል፡፡ ቁልፍ ዒላማቸው አድርገው የወሰዱት ደግሞ በአመራሩ፣ በሕዝቡና በወገን ጦር መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር፣ ፍርሃት እንዲነግስ የማሸበር ሥራ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲባባስ አብክረው የሚሠሩ እንደ ፌስቡክ አይነት የማኅበራዊ ሚዲያዎች የጠቅላይ ሚኒስትራችንን መዕልክቶች ከገፁ በመሰረዝ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ እንደ ሮይተርስ ያሉት ደግሞ በጠላት ያልተያዙ አካባቢዎችን እንደተያዙ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በተለያየ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ተላላኪዎቻቸው የፀጥታ ችግር እንዳለ በማስመሰል የግል ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ የማግባባት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በሕዝቡና በወገኑ ጦር ውስጥ ጥርጣሪዎችን ለመፍጠር የመንግሥት ባለስልጣናት ቪዛ እየጠየቁ ነው በሚል የውሸት ፕሮፖጋንዳ እየነዙ ነው፡፡ ከዲፕሎማሲ መርህ ውጪ የአንዳንድ ሀገር ኤምባሲዎች አዲስ አበባ እንደ ተከበበች በማስመሰልና ያሰቡት ውጥን እንዲሳካ በኤምባሲያቸው የሚሠሩ ዜጎቻቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡
መንግሥት በእንዲህ አይነት መንገድ ሀገርን ለማፍረስ የተጠመዱ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያሳሰበ በሀገር ጉዳይ ቀልድ የለምና ከድርጊቱ ባልተቆጠቡት ላይ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወስድ ያስጠነቅቃል፡፡
መላው ሕዝባችን ኢትዮጵያን የማዳን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የምንገኝ መሆኑን ተገንዝቦ የጀመረውን ሀገር የማዳን ንቅናቄ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ዋስትናችን ህልውናችንን በአንድነት ማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት በአፍራሽ ኃይሎችና ግብር አበሮቻቸው በኩል የሚነዙ የውሸትና መርዛማ ወሬዎቻቸው የሚመጡበት መንገድ በመዝጋት በአንድነት የመነሳቱን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
የኢትዮጵያውያንና የወዳጅ ሀገር ሚዲያዎች ለኅብረተሰባችን ትክክለኛውን መረጃ በወቅትና በተገቢው ጊዜ እንድታቀርቡ መንግሥት ይጠይቃል፡፡ በጊዜያዊ ድሎች መወራጨት የጀመሩትን የጥፋት ኃይሎች በማይናወጥ ዘላለማዊ ድሎችን በማስመዝገብ ወርቃማ ታሪክ መፃፍ ያለብን አሁን ነውና ሁላችንም በአንድነት እንቁም፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የታቀደልንና የተደገሰለንን ድግስ በጋራ በጣምራ ክንዳችን እንወጣዋለን፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊነታችን፣ ለአንድነታችን እና ለማንነታችን ሞት ክብራችን ነው! ከመስዋእትነት ውጪ ኢትዮጵያዊነት የለም!!
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት