
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1 የውጪ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ኹኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር የማይቻል ሲሆን፣ ማንኛውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው ይደነግጋል፡፡
በዚሁ አንቀጽ 2(ሀ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት በሚል ተደንግጓል ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባው ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ እንዲኾን አጽድቋል። በምክር ቤቱ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሀገሪቱ ካጋጠማት ችግር አኳያ የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ የሕግ ባለሙያ አቶ ሸጋው አለበልን አነጋግረናል፡፡
አቶ ሸጋው እንደገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተለመደው የሕግ ማስከበር ባለፈ ገደቦችን በማስቀመጥ የሽብርተኞችን እና የተላላኪዎቻቸውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ትልቅ አቅም አለው፡፡
አዋጁ የሀገርን ሕልውና ለመታደግ ሲባል የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳያስፈልግ ሽብርተኞችን በፍጥነት ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ነው የሕግ ባለሙያው የነገሩን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲንቀሳቀስ፣ አካባቢውን እና ሰርጎ ገቦችን እንዲከታተል ያስችላል፤ ሕግ አስከባሪው አካል ደግሞ ሕገ ወጦችን እንዲቆጣጠር ያስችላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ