
ባሕርዳር: ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በወረራቸው አካባቢዎች ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን ዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በችግር ውስጥ ይገኛል፡፡
የሽብር ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ከ110 በላይ እናቶች፣ ሕጻናት እና ተመላላሽ ታካሚዎች በምግብ፣ በውኃ እና በመድኃኒት እጦት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት፡፡ ኮሚሽነር ዘላለም እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ከዚህ በፊት ከዩኒሴፍ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶች ዳይሬክተሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚህም ባለፈ ችግሩ ባለበት አካባቢ በአካል ተገኝተው የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ ረድኤት ድርጅቶች ለተደረገው የድጋፍ ጥሪ ምላሽ አለመሥጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶች ሲቋቋሙ ሰብዓዊነትን መሰረት አድርገው እንጅ ዘርን፣ ቀለምን፣ ሃይማኖትን እና የፖለቲካ ልዩነትን መሰረት ባደረገ መልኩ አለመኾኑን ኮሚሽነር ዘላለም አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ረድኤት ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋት በሚፈቅድላቸው እና የተቋቋሙበትን መርህ መሰረት በማድረግ በጠላት ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን ከ5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየደረሰበት ካለው ስቃይ እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ግፊት እንዲያደርጉ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ