
ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ነዋሪዎች የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብለው አሸባሪውንና ወራሪውን የትግራይ ኃይል ለመፋለም ወደ ጦር ግንባር እየዘመቱ ነው። ወደ ግንባር ሽኝት የተደረገላቸው ዘማቾች እጅግ ከፍተኛ የማሸነፍ ወኔ፣ ሥነ ልቦና፣ ጀግንነት እና ቁጭት ይነበብባቸዋል።
ዘማቾቹ በቁጭት እንደገለጹት አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል በአማራ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ ሊበቃ ይገባል፤ ከእንግዲህ በኋላ አሸባሪውና ወራሪውን የትግራይ ኃይል የሚሸከም ትክሻ የለንም፤ አርሶ ማምረትና ወልዶ ማሳደግ የሚቻለው የአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ግብዓተ መሬት ሲፈጸም ብቻ ነው፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ካነጋገራቸው የእብናት ወረዳ ዘማቾች መካከል አቶ አምባው ጌትነት አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ወላድን እየገደለ፣ እየደፈረ እና የአርሶ አደሩን ሀብት እየዘረፈ መኖር የለበትም ብለዋል፡፡ ይህንን ወራሪ እና ሽብርተኛ ኃይል በአጭር ጊዜ ድባቅ በመምታት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ነፃ ለማውጣት ምለው ተገዝተው መነሳታቸውን አብራርተዋል።
ሌላኛው ዘማች ጸዳል ካሳ እንደገለጹት ነፃነቷን ጠብቃ ለዘመናት የኖረችውን ኢትዮጵያ በጡት ነካሹና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተወራለች፤ ሕዝቡ ከጫፍ እስከጫፍ በአንድነት ከተነሳ ግን አሸባሪ ኃይሉን በአጭር ቀን መደምሰስ ይችላል። ለዚህም በነቂስ መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
የእብናት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሙሉጌታ ይማም ነጻነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና ክብሯ የተጠበቀ ሀገር ከአያቶቻችን እንደተረከብን ለሚቀጥለው ትውልድም ከነነጻነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና ክብሯ ነው ልናስረክብ የሚገባው ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው ሕዝቡ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተፋልሞ ነጻ እንዳይወጣ የሐሰት ወሬ በሚያናፍሱ የውስጥ ባንዳዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ ይወሰዳል፤ እንዲህ ዓይነት ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ