
ባሕር ዳር: ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ሕግ አጽንታ መንግሥት መስርታ በኖረችባቸው አያሌ ዘመናት ሁሉ ከውስጥም ከውጭም ጠላት አጥቷት አታውቅም፡፡ በእነዚህ የፈተና እና የመከራ ዘመናት ሁሉ ኢትዮጵያ በአሸናፊነት እንድትወጣ እልህ አሰጨራሽ ውጣ ውረድ እና መስዋእትነት ተከፍሏል፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ከጉያዋ በወጡ ጠላቶች የሕልውና ፈተና ገጥሟታል፡፡
ወቅቱ ኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠል እና አማራ እንደሕዝብ የመኖር ወይም ያለመኖር ስጋት በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ተደቅኖበታል፡፡ የሕልውና አደጋውን ቀልብሶ እንደሕዝብ ለመኖር እና እንደሀገር ለመቀጠል በሀገር ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የአማራ ክልል ደግሞ የክተት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ይህንን አስመልክቶ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሕዝቡ ለክተት ጥሪ ያሳየው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው የዚህ ዘመን ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ በመድገም ሕልውናውን የሚያስከብርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና መንፈሳዊ ውድመቶችን እያደረሰ ነው ያሉት የቢሮ ኅላፊው ጅምላ ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈር እና መሰል የሰብዓዊ ቀውሶችም ደርሰዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ለሀገር ነጻነት መራር ዋጋ ከፍሏል፤ እየከፈለ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው አሁንም ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል የተቃጣበትን የሕልውና ሥጋት በላቀ ጀብድ እና ጀግንነት ይቀለብሳል ብለዋል፡፡ ለትግሉም ጽናትን እና ቁርጠኝነትን ስለሚጠይቅ በየደረጃው ካለው የዘርፍ መሪዎች ጋር መቀናጀት እና መናበብን እንደሚጠይቅም አውስተዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በሕልውና ዘመቻው ከሕዝቡ የሚጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባር መኖሩን ጠቅሰው የሚችለው በመዝመት፣ የማይችለው በሎጀስቲክ በመደገፍ እና አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡
በክተት ጥሪው ከመላው ሕዝብ የሚጠበቁ ጉዳዮች ያሏቸውን ዋና ዋና ነጥቦች አንስተዋል፡፡ ዘመቻውን በላቀ ጀብደኝነት፣ ጀግንነት እና ቁርጠኝነት መጋፈጥ ከሕዝቡ የሚጠበቅ ኅላፊነት ነው ያሉት አቶ ግዛቸው በጠላት ላይ የጋራ አቋም መያዝም ግድ ይላል ብለዋል፡፡ ጽናት እና ቁርጠኝነት የትግሉ መርህ መሆን አለባቸው ያሉት ኅላፊው በዚህ ጦርነት ያለን ብቸኛ አማራጭ ትግሉን ፊት ለፊት መጋፈጥ እና ማሸነፍ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ግዛቸው የክተት ጥሪውን የሚደግፉ አስገዳጅ ሁኔታዎች መቀመጣቸውን ገልጸው ሕዝቡ በጀመረው ቀና ትብብር እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠላት ከአውደ ውጊያ ይልቅ የሐሰት መረጃ እና ፕሮፖጋንዳን ስርጭትን አማራጭ የመታገያ መንገድ አድርጎ እየተጠቀመ መሆኑን ያወሱት ቢሮ ኅላፊው “ወቅቱ መረጃን አጣርቶ መልቀቅ ብቻ ሳይሆን መርጦ ማዳመጥንም ይጠይቃል” ብለዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና መረጃን ለሌሎች የሚያጋሩ አካላት ሕዝባዊ ኅላፊነት እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል ያሉት አቶ ግዛቸው ከድርጊታቸው በማይታቀቡ አካላት ግን ለሕዝብ እና ለሀገር ደኅንነት ሲባል መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም አስታውቀዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በየአካባቢው ሕዝቡ ለመንግሥት እና ለጸጥታ ኃይሎች የሚሰጠው መረጃ ችግሮችን ለመቆጣጠር ጉልበት መሆኑን ጠቁመው ከዚህ በበለጠ መንገድ መናበብ፣ ኅላፊነት መውሰድ እና ሀገርን መታደግ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ