ለሀገርህ ምንም ነገር አትሰስት

152
ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ከምንም ከማንም በላይ ናት። በሰበብ አትሸጥም፣ በጥቅም አትለወጥም። በሚመችም በማይመችም ጊዜ ሁሉ እናት ናት። ሲደላ መኖሪያ፣ ሲከፋ መሸሸጊያ፣ ሲሞቱም መቀበሪያ ናት። ሀገር የሌለው እንኳን ሕይወቱ አስከሬኑ ማረፊያ የለውም። እንደዘበት ይጣላል። እንደቀልድ በአንዱ ይቀራል።
ሀገር ክብር ናት፣ ታሪክ ናት፣ ሕይወት ናት፣። ሀገር ከሌለ ምንም የለም። እንደ ልብ መናገር፣ እንደፈለጉ ሰርቶ፣ ኮርቶ ለመኖር ሀገር ያሻል። ሁሉም ነገር እንዲኖርህ ከፈለክ፣ ሀገርህ እንድትኖር፣ ጣር፣ ሁሉንም ነገር ማጣት ከፈለክ ግን ሀገርህ ስትፈልግህ ጥለህ ትሸሻለህ፣ ምክንያት ታበዛለህ፣ ስበብ፣ ትደረድራለህ፣ ለሀገርህ ሰበበኛ አትሁን፣ ሁልጊዜም ሀገርህን ከምንም ነገር አስቀድም። ሰበበኛ ከሆንክ ሀገር አልባ ሆነህ ትቀራለህ።
ኢትዮጵያዊ ከሆንክ መሸነፍ ይመምህ፣ መደፈር እንቅልፍ ይንሳህ፣ ለኢትዮጵያዊ መደፈር፣ አንገት ደፍቶ መኖር አልተገባም። በዘመናት የታሪክ ጉዞ ኢትዮጵያዊ ጠላትን አንገት አስደፍቶ እንጂ በጠላት አንገት ደፍቶ የኖረበት ዘመን የለም። ጠላት ሲመጣ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ እየተነሱ፣ ወደፊት እየገሰገሱ ነው የተከበረች ሀገር፣ ያልተደፈረች ምድር ያስረከቡን። እነርሱ ለሀገር ሰበበኛ አልነበሩም። ልዩነት ከኢትዮጵያዊነት አያጎድላቸውም፣ በአንድ ለመነሳት አያግዳቸውም፣ ለጠላት በር አይከፍትባቸውም፣ ከማሸነፍ አያስቀራቸውም፣ ድል አይከለክላቸውም። ልዩነታቸው ጌጣቸው፣ የፍቅር መገለጫቸው፣ የማሸነፊያ ምስጢራቸው ነው።
ኢትዮጵያ የጋራ ቤት፣ የጋራ ጌጥ፣ የጋራ ክብር ናትና። አበው ፈሪ ጮማ አይቆርጥም ቢቆርጥም አይጣፍጥለትም ይላሉ። ጀግና ነው ሁሉ ነገር የሚጣፍጥለት፣ የሚያምርለት፣ ፈሪ ከሆንክ የመጣው ሁሉ ይንቅሃል፣ ይረግጥሃል፣ ይደፍርሃል፣ ከሰው በታች ትኖር ዘንድ ይፈረድብሃል፣ ደፋር ስትሆን ግን ሁሉም ያከብርሃል፣ በአገኘህ አጋጣሚ ሁሉ እጅ ይነሳልሃል፣ አንቱ ይልሃል። የሚኮራበት እንጂ የሚታፈርበት ልጅ አትሁን። የሚኮራበት ልጅ ከሆንክ አባትህ ይመርቁሃል፣ እናትህ ይደሰቱብሃል፣ ይመኩብሃል፣ የሚታፈርበት ከሆንክ ግን ቤተሰቦችህ ያዝኑብሃል፣ የሚከተልህ ትውልድ ያፍርብሃል። የሚያኮሩ አባቶች ስለነበሩን ኮርተን ኖረናል፣ ተከብረን ዘመናትን አሳልፈናል። ታሪካችንን ላገኘነው ሁሉ ለመናገር ተቻኩለናል። የሚያኮራ ታሪክ ቢነግሩት ያምራል፣ ቢያነሱት ያስከብራልና።
በተከበረች ሀገር የኖርነው የሚያኮራ ታሪክ የተቀበልነው፣ የሚያስፈራ ግርማ የተላበስነው አባቶቻችን ጀግኖች ስለነበሩ ነው። የጀግና ልጅ ስትሆን ሁሉም ጠላት ይፈራሃል። ጎረቤትህ ለፍቅር እንጂ ለጠብ አይመኝህም። በዘመናት ሂደት ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው ሁሉ አንደኛውም ያሰበውን አላሳካም። ይልቁንስ በኢትዮጵያ ምድር አፈር በልቶ ቀረ እንጂ።
የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ለሀገር የሚሰስቱት፣ የሚቆጥቡት ነገር አልነበራቸውም፣ ሀገር እውቀት በፈለገች ጊዜ እውቀት፣ ሀብት በፈለገች ጊዜ ሀብት፣ ጉልበት በፈለገች ጊዜ ጉልበት፣ ሕይወት በፈለገች ጊዜም ሕይወት ሰጥተዋታል። ኢትዮጵያ ጠይቃቸው የከለከሏት፣ ኢትዮጵያ ጠይቃቸው ያልመለሱላት፣ ኢትዮጵያ ጠይቃቸው እምብኝ ያሏት፣ ኢትዮጵያ ጠይቃቸው የደበቋት ነገር የለም። ለጥያቄዋ መልስ ሰጥተዋል፣ ለጭንቋ ቀን ደርሰዋል።
ለሀገር ሰበበኞች አንሁን፣ ሰበብ ካበዛን የምንወዳትን እንነጠቃለን፣ የነበረንን እናጣለን፣ አደራችንን እንበላለን፣ ታሪካችንን እናበላሻለን፣ ከእኛ ቀጥሎ ለሚመጣው ትወልድ ማፈሪያ እንሆናለን። ለዓድዋ ዘመቻ ሰበብ ያላበዙት ኢትዮጵያውያን ሀገር አትርፈዋል፣ ትውልድ አኩርተዋል፣ የጥቁርን ዘር አስደስተዋል፣ ከታሰረበት ቀንበር አስፈትተዋል፣ የበደለኞችን ግንብ አፍርሰዋል፣ የሰውን ልጅ እኩል አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ዓድዋ የሰበሰባቸው በአንዲት አዋጅ የተሰማች የእናት ሀገር ድምፅ ናት። እናት ስትጣራ አርፎ የሚተኛ የለም። ከጭንቋ ሊደርስላት፣ ከውርደት ሊታደጋት፣ ያንዣበባትን የክፉ ቀን ደመና ሊያስለቅቅላት፣ ተስፋዋን ሊያለመልምላት፣ ወዘነዋን ሊመልስላት፣ ብርሃኗን ሊያመጣላት ይገሰግሳል እንጂ። እናት ስትጣራ ልጅ ዝም ካለ ማሕፀኗ ይረግመዋል፣ እትብቷ ይወቅሰዋል፣ በዚያ ዘመን በአንዲት አዋጅ የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያን ሕይወት ሰጥተው ሀገር አቆይተዋል፣ ነብስ ገብረው ታሪክ ሰርተዋል፣ አጥንት ከስክሰው ትውልድ አኩርተዋል፣ ደም አፍስሰው ነፃነትን ከተራራው አናት ላይ ከፍ አድርገው ሰቅለዋል።
እነሆ ያ ዘመን አለፈ፣ ሌላ ዘመን መጣ፣ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የተሸነፈው ጠላት ኀይል አሰባስቦ ተመለሰ። ኢትዮጵያውያን ሰለቸን፣ ደከመን ሳይሉ ታገሉት፣ ክንዳቸውን አቀመሱት፣ በሳንጃቸው ወጉት፣ በጦራቸው ሰቀዙት፣ ምድራቸውን እሾህ አደረጉበት፣ መውጫ መግቢያ አሳጡት፣ አልሆን ሲለው፣ ለኢትዮጵያውያን ሌላ ከፍ ያለ ታሪክ ትቶ፣ የራሱን ታሪክ ዳግም አበላሽቶ ተመለሰ። ብዙውም የኢትዮጵያ አፈር በላው። ልብ ይበሉ በዚህ ዘመን ንጉሡ አልነበሩም። ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፣ እሳቸው በተሰደዱበት ሀገር ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራዎችን ቢሠሩም ከአርበኞች ጋር ግን አልነበሩም። አርበኞች ለሀገራቸው ምክንያት አልደረደሩም፣ ንጉሡ የሌሉባትን ሀገር እንዋጋላትም አላሉም። ሀገራቸውን ከንጉሡ ጋር አላወዳደሩም። ሀገር ክብር ናት፣ ሀገር እናት ናት፣ ሀገር ሕይወት ናት በማንም የማንለውጣት፣ ከማንም ጋር የማናወዳድራት ብለው ተነሱ፣ ጠላትን እጅ አስነሱ፣ ልብ ይበሉ በዚያ ዘመን ጀግኖች አርበኞች ሰበብ ደርድረው፣ ወደ በረሃ መውረድ አቁመው፣ የመጣውን ይሁን ብለው ቢቀበሉ ኖሮ ዛሬ ላይ ታሪኳን የተነጠቀች ሀገር ትኖረን ነበር። እነርሱ ግን ሕይወት ሰጥተው ሀገር አኖሩ፣ ትውልድንም አኮሩ። ከብረው አስከበሩ።
ሀገርህ ስትጠራህ በሚመችም በማይመችም ጊዜ ሁሉ አለሁ በላት። ድምጿን ስማት። ጉልበት ካለህ ተዋጋላት፣ ገንዘብ ካለህ ስጣት፣ መዝመት፣ ሀብት መስጠት ካልቻልክ ወደ ሚወዳት ፈጣሪዋ ፀልይላት። አንዱንም ግን አትንፈጋት። መሪህ ቢያስቀይምህ፣ ችግር ቢበዛብህም ሀገርህን ከማዳን ግን አትስነፍ።
እምዬ ምኒልክ ያስነገሩት አዋጅ ዛሬም ተደግሟል። የልጆቿን መሰባሰብና ጠላትን በጋራ መምታት የፈለገችው ኢትዮጵያ ከዘመናት በኋላ ዛሬም ጠርታለች። ኑ እና ከጉያዬ የበቀለውን ክፉ አረም ንቀሉልኝ ብላለች። በእኔ ዘመን ታሪክ ሰርቼ አልፋለሁ፣ ሀገሬንም እታደጋለሁ፣ የእናቴን ጥሪ እሰማለሁ የሚል ሁሉ ጠላት ወደመጣበት ይዝመት፣ በእርሱ ዘመን በተዘጋጀው የታሪክ መፃፊያ ድርሳን ይፃፍበት፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ ይጨምርበት። ዛሬ ላይ በአንተ ዘመን በቀረበው የታሪክ ብራና ላይ ታሪክህን ባታሰፍርበት፣ ከአንተ ቀጥሎ የሚመጣው ትውልድ የሚያነበው ያጣል፣ የኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክም ይቋረጣል። የተከበረ ሞትን እንጂ የተዋረደ ሕይዎትን አትመኝ። በዘርህ የሚያስፈራ እንጂ የሚፈራ እንደሌለ ልብ በል። ፈርተህ ከሸሽህ፣ ሀገርህ ጠርታህ ከቀረህ የአባቶች አፅም ይወቅስሃል፣ ታሪክ ይታዘብሃል፣ እንደ ጀግና የክብር ሞት ሙት እንጂ በፍርሃት የተከበበች ነብስ እንድትኖርህ አትምረጥ።
በባርነት ከመኖር ለነፃነት፣ ስለ ነፃነት በነፃነት መሞት ክብሩ ከፍ ያለ ነው። ከትግራይ የተነሳውን ጠላትህን ተናንቀህ አጥፋው፣ ዛሬ ላይ ክንድህን አሳዬውና እርሱን የሚከተሉ በእርሱ ጥላ ሥር መኖር የሚሹ ጠላቶችህ ሁሉ ይግረማቸው። ሀገርህን ወሮ፣ ቀየህን ደፍሮ ዝም ካልክ ግን ነፃ በሆነች ምድር በፈቃድህ ባርያ ሆነህ ትኖራለህ።
“እምዬ ኢትዮጵያ ኩሪ ይገባሻል
የማያስደፍርሽ ጀግና ልጅ ወልደሻል” እያልክ ወደፊት ገስግስ፣ ሀገርህ የምትኮራው አንተ ስትዘምት ነው። ዝመትና ሀገርህን አኩራት፣ ዝመትና በጭንቅሽ ቀን አለሁ በላት፣ ዝመትና እኔ እያለሁ ማንም አይደፍርሽም በላት፣ ጠላቷን አጥፋላት፣ ቀዬዋን ሰላም አድርግላት። የጀግና ልጅ ጀግና ሁን። ያለማሃቸው ከተሞች ወድመው፣ ያሳደካቸው ልጆች በግፍ ተደፍረው፣ በአደጉበት ቀዬ በሮጡበት መስክ እንዳትኖሩ ተብለው ዝም ካልክ ነፃነትን ሸጠህ ባርነትን ልትገዛ ወድደሃል ማለት ነው።
ኢትዮጵያን ዝም ብሎ መስጠት የዓለምን መሠረት ማናጋት፣ የሰውን ልጅ መገኛ ማሳጣት፣ ጥበብን ማጥፋት፣ የጀግኖችን ታሪክ ማበላሸት፣ ዓድዋን መርሳት፣ ነፃነትን መሸጥ፣ አሸናፊነትን መለወጥ ነው። ተሸንፋ የማታውቅ ሀገር በዚህ ዘመን እንድትሸነፍ አትፍቀድ፣ ለኢትዮጵያ ማሸነፍ ብቻ ልኳ መሆኑን አስብ።
ለአሸናፊነት የተፈጠረች ለክብር የታደለች፣ ከሁሉም የቀደመች፣ ጠላትን በመቅጣት የታወቀች ሀገር መሆኗን አትርሳ። ጀግና ሕዝብ የወለደህ፣ ያሳደገህ ነህና በጀግንነት ተዋደቅ። እንደ ቀደሙት አባቶች የጠየቀችህን ሁሉ አድርግላት። ምንም ነገር አትሰስታት።
ኢትዮጵያ ዝም ብላ አልቆመችም፣ ደም ተከፍሎባት፣ አጥንት ተከስክሶባት፣ ሕይወት ተገብሮላት ነው። ነገ በታሪክ እንድትታወስ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ ደምህን አፍስስ አጥንትህን ከስክስ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የተፈናቀሉ የዳህና ወረዳ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመሩ።
Next articleነገ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተዘጋጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተገለጸ።