በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የተፈናቀሉ የዳህና ወረዳ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመሩ።

277
ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ከቀያቸው ተፈናቅለው በእብናት ወረዳ ተጠልለው የነበሩ የዳህና ወረዳ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ኃይል ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከተለያዩ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በእብናት ወረዳ፣ በባሕር ዳር ዘንልማ ቀበሌ፣ በሳህላ ሰየምት ወረዳ እና በሌሎችም አካባቢዎች በጊዜያዊ መጠለያ አስቸጋሪ ሕይወት እያሳለፉ ይገኛሉ።
አሸባሪው ኃይል ወረራ ፈጽሞ በነበረባቸው አካባቢዎች ያሉ ወገኖችን የዕለት ምግብ በመዝረፉ በርሃብ ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን አሚኮ ከሰሞኑ በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል።
ከዳህና ወረዳ የተፈናቀሉ ወገኖች አሁንም ተጨማሪ ህልፈት፣ የሃብት ውድመት እና ዘረፋ እንዳይፈጸም ወደ ቀያቸው ተመልሰው መራር ትግል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
አቶ ተምረው አበጀ የዳህና ወረዳ ነዋሪ ናቸው። የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ በፈጸመው ታላቅ ጀብድ አሸባሪው ኃይል አካባቢውን ለቆ ፈርጥጧል ብለዋል። እሳቸውም የትግሉ ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፎ በሙሉ አቅሙ በመፋለም ወራሪ ኃይሉም በአጭር ቀን የዋግ ምድርን ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻል መሆኑንም ከተፈጸመው ጀብድ ተነስተው ነግረውናል።
ሌሎች አካባቢዎችን ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ነጻ ለማድረግ መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተቀብለው ሕዝባዊ ማዕበልን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶችም ጠላትን ለመፋለም የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሕዝባዊ ማዕበሉ መቀላቀል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሃይማኖት አለልኝም የዳህና ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ወራሪው ኀይል ግፍ መፈጸሙን ተናግረዋል። በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ድባቅ ተመትቶም ከወረዳው ፈርጥጧል ነው ያሉት።
ይህ ወራሪ ኃይል የሠራውን ግፍ መመለስ የሚቻለው ደግሞ የዋግ ምድርን መቀበሪያው በማድረግ ነው፤ ለዚህም ኹሉም ሊዘምት ይገባል፤ እኔም ለመዝመት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ሕዝባዊ ማዕበሉ ተፋፍሞ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
በእብናት ወረዳ የተጠለሉት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሕዝባዊ ማዕበሉን እንዲቀላቀሉ እያስተባበሩ የሚገኙት የዋግ ልማት ማኅበር (ዋልማ) ኀላፊ መለሰ ባየ እንደገለጹት በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወጣቶች ጠላት ወደአለበት ቦታ ሂደው እንዲፋለሙ እየተደረገ እንደሆነ ነው ያብራሩት።
የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ሕጻን በመግደል አራስ እናቶችን አስገድዶ ደፍሯል፤ የግልና የመንግሥት ሀብት ዘርፏል፤ ቀሪውን አውድሞ ሂዷል ብለዋል። ወጣቱም እናቱ እህቱና አጠቃላይ ቤተሰብ ሲደፈር ቆሞ ከማየት ሊወጣ ይገባል፤ የሕይወት መስዋእትነትንም ሊከፍል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መሪዎችም ግንባር ቀደም በመሆን ጦርነቱን ለመምራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ ፦አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleአዲሀገራይ የሚገኘው አዲቡክራይ የአሸባሪው ትህነግ ማሰልጠኛ ማዕከል በአየር ኃይል ተመታ።
Next articleለሀገርህ ምንም ነገር አትሰስት