ዓመት የሞላው ክህደት።

167
ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዛሬ ዓመት ከተሰነዘረባቸው ጥቃት ተርፈው ግንባር ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአጭር ጊዜ ሀገሪቱን ነጻ በማውጣት የሕዝቡን ያለመሸነፍ ታሪክ ዳግም እናበስራለን ብለዋል፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲያገለግል የኖረውን፣ በጋብቻ የተቆራኘውን፣ ከሚጎርሰው ቆርሶ ያጎረሰውን ወታደር ሀገር አማን ብሎ ባረፈበት የአሸባሪው ስብስብ ከጀርባው አጠቃው። በወታደራዊ ሳይንስ የተማረከ የማይገደል ቢሆንም የፍርሃቱ ጥግ አይሎበት ባዶ እጃቸውን የነበሩ የሠራዊት አባላትን በሚዘገንን ሁኔታ ገደለ፡፡
መቶ ዓለቃ ስንታየሁ ግዛው ተዓምር በሚያስብል መልኩ ሕይወታቸው የተረፈ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው። በወቅቱ አዲግራት ግዳጅ ላይ የነበሩት መቶ አለቃ ስንታየሁ የሆነውን በቁጭት አስታውሰው ነግረውናል፡፡
ሠራዊቱ ግዳጁን ፈጽሞ ረፍት ላይ እያለ ከምሽቱ 4፡00 ገደማ መብራት ጠፋ፣ የስልክ ግንኙነትም ተቋረጠ፤ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከወትሮው የተለዬ እንቅስቃሴ መታዬትም ጀመረ፤ በሠራዊቱ ላይ ክሕደት ይፈጸማል የሚል ሀሳብ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ቀጥለው ከሌሊቱ 6፡00 ገደማ ተኩስ መሰማት ጀመረ፡፡
ተረኛ የሠራዊት አባላት ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ቢደረግም ከትግራይ ማህጸን የተፈጠሩ ትላልቅ የሠራዊት አባላት ክሕደት ማሳዬት ጀመሩ፡፡ ጥበቃዎችን ከምሽግ አስወጥተው ትጥቃቸውን አስፈቱ፤ በአንድ ዓላማ ለዓመታት አብረን የተሰለፍን የሠራዊት አባላትም ለጥቃት አሳልፈው ሰጡን፡፡
በነጋታው ያዘጋጁትን ልዩ ኀይል አግበስብሰው የወታደሩን ካምፕ ወረሩ፣ በሠራዊቱም ላይ ተኩስ ከፈቱ፡፡ አካባቢውም በከሃዲዎቹ ታጣቂዎች ተሞላ፤ ከዚያም የሠራዊት አባላቱን ወደ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል እንደወሰዷቸው አንስተዋል፡፡
እሳቸውን ጨምሮ ከምክትል መቶ አለቃ እስከ ጀነራል ማዕረግ ያላቸውን የጦር መሪዎች ደግሞ አባላቱን አስተባብረው አደጋ ያደርሱብናል በሚል ስጋት በሌሊት ወደ ተንቤን በርሃ እንደወሰዷቸው ያስታውሳሉ፡፡
የሚበላ እና የሚጠጣ በሌለበት ረጅም የእግር ጉዞ አደረጉ፤ በዚያ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ወደሚፈለገው ቦታ ሲደርሱም ሊቀበሩበት የተዘጋጀ ዶዘር እና ጉድጓድ ነበር ያገኙት፡፡ ይሁን እንጂ ተዓምራዊ በሆነ መልኩ ነገሮች በቅጽበት ተለዋወጡ፤ ከእርሱ በላይ አሸናፊ፣ ጦር አዋቂ የለም ብሎ የታበየው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ተርበተበተ፤ መድፎች ሲያጓሩ ተሰማ፤ ቅምቡላ በቅርበት መውደቅ ጀመረ፤ የእናት ጡት ነካሾች ቀቢጸ ተስፋም ከሰመ፤ ሠራዊቱን ለመቅበር ያዘጋጁትን ጉድጓድ እና ዶዘር ጥለው ወደ ጫካ ፈረጠጡ፡፡
የወገን ጦር እንደ አንበሳ እያገሳ፣ እንደ አራስ ነብር እያጉረመረመ ለተሰነዘረበት ጥቃት አጸፋ እየሰጠ ታፍነው ወደነበሩት አባላት ከተፍ አለ። መላው ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብሎ ከጠላት ጋር ተፋለመ። ጠላት ተፍረከረከ።
ከኢትዮጵያዊ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ዕሴት እና ማንነት ያፈነገጠው ኢሰብዓዊ ድርጊቱ ሀገር እና ሕዝብን ለማገልገል ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በተሰባሰቡ ጀግኖች ላይ ብቻ አላበቃም፡፡ የትግራይን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባሳለፈ ማግስት ጠላት ተሰባስቦ ዳግም የጥፋት በትሩን በንጹሃን ላይ ማሳረፍ ጀመረ።
ማይካድራ ላይ ጅምላ በመጨፍጨፍ የተጀመረው ዘግናኝ ግፍ በጭና፣ በውርጌሳ፣ በቆቦ፣ በአጋምሳ፣ በኮምቦልቻና በጋሊኮማ አካባቢዎች ተፈጽሟል፡፡ አሸባሪው ኀይል በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሀብት ተዘርፎ ወደ ትግራይ ተጭኗል፤ እንዲወድምም ተደርጓል፡፡
እንስሳትን ሳይቀር በጅምላ የገደለው አረመኔ አሁንም ግፉን ቀጥሏል፡፡ ሠራዊቱም ይህንን ለመቀልበስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር እየተዋደቀ ይገኛል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ክህደቱ በፈጠረበት ቁጭት እንደ ንሥር እየተወረወረ ጠላትን የሚያጠቃ ትንታግ ሆኗል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመ ጊዜ በአጭር ጊዜ በዛላምበሳ ግንባር መቀሌን በተሻለ የግዳጅ አፈጻጸም የተቆጣጠረው የጦር አባል የነበሩት ሻለቃ አንተነህ ከፈለኝ ሠራዊቱ አሁንም በጀግንነት እየተፋለመ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ቆስለው እንኳን የማገገሚያ ጊዜ ሳያስፈልጋቸው በወኔ ከጠላት ጋር የሚፋለሙ እንቁ አናብስት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ያነጋገራቸው የሠራዊት አባላት “ትውልድ እንዲቀጥል የሀገር ሕልውና መረጋገጥ አለበት” ብለዋል። ለዚህም ሠራዊቱ በጋለ ሀገራዊ ስሜት ጠንካራ ክንዱን በጠላት ላይ ማሳረፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ጠላትን በተባበረ ክንድ ከማጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ያሉት የሠራዊት አባላቱ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ግንባር ድረስ በመሰለፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ ኀይል መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“መታገል እየቻለ እቤቱ ቁጭ ብሎ ትግሉን የሚመለከት ሰው መኖር የለበትም” የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን
Next articleአዲሀገራይ የሚገኘው አዲቡክራይ የአሸባሪው ትህነግ ማሰልጠኛ ማዕከል በአየር ኃይል ተመታ።