
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያውን የሰጡት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን በኹሉም ከተማዎችና ወረዳዎች ሕዝቡ ንቅናቄ በመፍጠር፣ የመንግሥትም ኾነ የግል ትጥቅ ያላቸው ኹሉ ወደ ግንባር እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። የሕዝቡን ማእበል በመጠቀም አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግሥት ባስተላለፈው የክተት ጥሪ መሰረት የዞኑ ሕዝብ ዳግም የትግል ስሜቱ ግሎ መቀጠሉን ተናግረዋል። “በእኛ ግንባር በእማወራ ወይም በአባወራ ደረጃ ቢያንስ አንድ ሰው መውጣት እንዳለበት ተወስኗል። መታገል እየቻለ እቤቱ ቁጭ ብሎ ትግሉን የሚመለከት ሰው ግን መኖር የለበትም” ብለዋል። ይኹን እንጂ ሕዝቡ ያለ ጉትጎታ ለትግል የመሰለፍ ፍላጎት እንዳለውም አቶ ያለዓለም ጠቁመዋል።
ዞኑ ጠላትን ሙሉበሙሉ ለመደምሰስ የሚያስችል ሕዝባዊ ማእበል ማንቀሳቀስ መጀመሩን ነው የተናገሩት። “ማንኛውም ዘማች ወታደራዊ አመራሩ በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት በመመራት ጠላት በሚመታበት ሁኔታ እንዲኾን ተወስኗል” ነው ያሉት። የሕዝብ ማእበሉ በምን መልኩ እንደሚታገል፣ ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ በአመራሩ ይመራል ብለዋል።
በተለያየ ምክንያት ወደ ዘመቻው የማይሄዱ ሰዎች በከተሞችና በሚያስፈልጉ ቦታዎች ተመድበው ጸጥታን የማስከበር ተግባር እንደሚፈጽሙ ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል። የጠላት ተላላኪ ሊኾኑ የሚችሉ ሰዎችን የመለየት ተግባር የሚፈጽም የጸጥታ አካል የተመደበ መኾኑንም ተናግረዋል።
ከዞን ጀምሮ በየደረጃው የተዋቀረው አዲሱ አመራር ትግሉን በተሳካ መልኩ ለማራመድ እንደሚያስችለው አቶ ያለዓለም ጠቁመዋል። አካባቢውን በሚገባ የሚያውቁና ጥሩ ሥነምግባር ያላቸው መሪዎች ለትግሉ የተመደቡ እንደኾነ ነው ዋና አስተዳዳሪው ያብራሩት። የጠላት ፍላጎት አማራን ማጥፋትና ኢትዮጵያን ማፍረስ ስለኾነ ጠላትን ከተወሰነ አካባቢ በማጥፋት በሚገኘው ድል መኩራራት ሳይኾን ጠላት ሙሉበሙሉ የሚጠፋበት ግብ መቀመጡን አቶ ያለዓለም ገልጸዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት አሁን የሚሰለፈው ሕዝባዊ ማእበል ጠላትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት የሚያስችል ነው። የሕዝብ ማእበሉ ዓላማ ማንነትን የሚያስከብር፣ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ መኾን እንዳለበት ተናግረዋል። “አመራሩም ኾነ ሕዝቡ መገንዘብ ያለበት ቁምነገር ለነፃነታችን ካልታገልን ለባርነት ዋጋ እንከፍላለን” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ