
ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ለዘመናት በቆዬ ጥላቸው ተነስቶ አማራን ለማጥፋት፣ ኢትዮጵያን ለመበተን በወረራ ላይ ነው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ወራሪና አማራን ወርሯል፣ ዜጎችን በግፍ ገድሏል፣ ሀብቱን ዘርፏል፣ ያልቻለውን አውድሟል።
ወራሪና ዘራፊውን ኃይል ለማጥፋት፣ የተያዙ አካባቢዎችንም ነፃ ለማውጣት የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ጥሪ አስተላልፏል። የፌዴራል መንግሥቱም ዜጎች የኢትዮጵያን ጠላት ለማጥፋት እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል።
የአማራ ክልል ሕዝብም የተከፈተበትን ወረራ ለማስቆም በተጠራው የክተት ጥሪ መሠረት እየተመመ ነው። ለሕልውናው ስለተጠራው የክተት ጥሪ ሐሳባቸውን የሰጡን በደቡብ ወሎ ዞን የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ለዘመቻው ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የካራማራ ዘማች ዋሲሁን ከበደ በካራማራ ጦርነት ከሶማሊያ ጋር ተናንቀን ሀገር አትርፈናል ሲሉ ነው ያስታወሱት። በጊዜው ከጠላት ጋር ተናንቀው ሀገር ያተረፉት ዘማች ዛሬም ለሕልውና ተኝቶ የሚያድር አለመኖሩን ተናግረዋል።
❝እኛ የጀግና ልጆች ጀግኖች ነን፣ ታሪካችን አይበላሽም ጠላትን ድባቅ መትተን የጀግንነት ታሪካችንን እናስቀጥላለን❞ ብለዋል። ሀገር ከሌለች ኹሉም ነገር እንደማይኖር ነው የገለፁት። ሕዝቡ በጀግንነት ለመዋደቅ ዝግጁ ነው፤ በሀገር ላይ ቀልድ የለም ነው ያሉት። ወርደህ አንክተው በሚል የሚሊሻ ሠራዊት ውስጥ በካራማራው ጦርነት መዋጋታቸውን ያስታወሱት ዋሲሁን በዚያ ወቅት የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ከጠላት ጋር አብረው ወግተውናል ሲሉም ያስታውሳሉ። እነርሱ ከባንዳነት የዘለለ ታሪክ እንደሌላቸውም ገልፀዋል።
የክተት ጥሪውን የተቀበለው አሰፋ ረታ ለውጊያ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። እንደ ሕዝብ ተነስተን የአሸባሪውን ወራሪ ኃይል እናጠፋዋለንም ነው ያለው። ሀገር ተወሮ ክብር ተደፍሮ አርፎ የሚቀመጥ እንደማይኖርም ተናግሯል።
ወንድዬ ሃምዛ የክተት ጥሪው ወጣቱን በወኔ የሚቀሰቅስ መሆኑን ነው የገለፀው። የክተት ጥሪውን ሰምተው የተለያዩ አደረጃጀቶችን መሥራታቸውን ነው የተናገረው። የተነሳሳውን ወጣት በማሰማራት ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ መታገል እንደሚገባም ተናግሯል።
አማራ በአንድነት ተነስቶ ጠላቱን ማጥፋት አለበት ያለው ወንድየ አማራ በአንድነት እና በወኔ ተነሳ ሲባል ገና ጠላት እንደሚርድ ነው የገለፀው። ኹሉም ግንባር ለመግባት ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል።
ሌላኛው ነዋሪ ደሳለው አባቡ የክተት ጥሪው መልካም ውሳኔ መሆኑን ገልጿል። ከክተት ጥሪው በፊት በርካታ ተጠባባቂ ኃይል እንደነበር የተናገረው ደሳለው የክተት ጥሪው መሰማት ደግሞ የበለጠ ኃይል የሚፈጥር ነው ብሏል።
በዚህ ወቅት ኹሉም በአንድነት ኾኖ ጠላቱን መታገልን ማጥፋት እንደሚገባው ተናግሯል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል በምን አቅሙ ያሸንፍናል? ሲል የሚጠይቀው ደሳለው የአማራ ግርማ የሚደፍር አይደለም ነው ያለው።
ችግሮቻችንን ከድል በኋላ የሚፈቱ ናቸው፤ አሁን የጋራ ጉዳያችን ጠላትን መደምሰስ ብቻ ነው ያለው ። ዛሬ ላይ ጠላትን መደምሰስ ካልተቻለ የአማራ ታሪክ ይጠፋል፤ ነገም መኖር አይችልም ሲል ነው ያሳሰበው። ወጣቱ በምንም አይነት አሉባልታ መፈታት እንደማይገባም ገልጿል።
በየትም ይሁን በየትም አማራ በአንድነት ተነስቶ ጠላትን ድባቅ መምታት ይገባዋል ብሏል። አማራ በጋራ ተነስቶ የዘመተ ቀን፣ የሚመልሰው አለመኖሩንም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ