
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በዓላማችን በተደረጉ ጦርነቶች በጦር ስልታቸው በታሪክ የማይረሱ ነገሥታት አልፈዋል። ከእነዚህ ነገሥታት ውስጥ አውሮፓን እንደ አንድ ሀገር የገዛት ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ ተደርጎም ይነገርለታል፤ በሚያሳየው የጦርነት ስልት እና የአመራር ችሎታው “በጦርነት ጀግናና ጥበበኛ ወታደር” ፣ በስትራቴጂው “ወደር አልባ ጀነራል”፣ በመንግሥት አመራር ችሎታው “ረቂቅ ፖለቲከኛ” ወዘተ እየተባለ በታሪክ ይዘከራል፤ የፈረንሳዩ ቀዳማዊ ናፖሊዮን ቦናፓርት።
ኀያልነቱ በጦር ሜዳ ውሎ የተመሰከረለት ይህ ሰው “የእያንዳንዱ ሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሚገነባው ምሽግ ነው” የሚል መርህ ያራምድ ነበር።
ወታደሮቹ ከጀግናም ጀግና እንዲሆኑ ደግሞ “ለመሞት የወሰንን ቀን ጀግኖች ሆነናል፤ ሁላችንም ለመሞት የተፈጠርን ነን፤ የጥቂት ቀናት ዕድሜን መጨመር ደስታ ይሰጠናል ብላችሁ አትሞኙ” ይላቸው ነበር።
“ጀግናን ጀግና የሚያደርገው ሞቱ ሳይሆን የሞተበት ምክንያት ነው” በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ናፖሊዮን ፈረንሳይ በታሪኳ ዓይታ የማታውቀውን ጀግኖች ሲያመርትላት ኖሯል፤ የማትደፈር ሀገርም አድርጓት አልፏል።
በኢትዮጵያ ያለፉት መንግሥታት እንደ ሴረኛው እና ሽብርተኛው ትህነግ ጎሳን ወይም መንደርን መሰረት ያደረገ አገዛዝ ከመከተል ይልቅ ለኢትዮጵያዊነት የጎላ ትኩረት በመስጠታቸው በሀገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና አበርክተው ማለፋቸውን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አዳነ ካሴ ነግረውናል፡፡
ይህ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተገነባው ማንነት በየጊዜው በሀገሪቱ ላይ የተቃጡ ወረራዎችን በአንድነት ለመመከት ማስቻሉን ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ ያነሱት።
በጣሊያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሀገርን ላለማስደፈር ያደረጉት ተጋድሎ አንዱ ማሳያ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል። ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጃ ወደ ግዛቷ ዘልቃ መግባቷን ተከትሎ አጤ ምኒልክ ከመኳንንቱና ከሹማምንቱ ጋር በመመካከር በጦርነት ለመፋለም መስከረም 1887 ዓ.ም አዋጅ ማስነገራቸውን ገልጸዋል። አዋጁም ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግራቸውን እና ቅራኔያቸውን ወደ ጎን በመተው ሃይማኖትን እና ሀገርን ሊያጠፋ የመጣን የውጭ ወራሪ በጋራ ለመመከት የተላለፈ ጥሪ እንደሆነ ነው ረዳት ፕሮፌሰር አዳነ ያነሱት። በዚህም ከሹማምንቱና ከሕዝቡ በጎ ምላሽ አግኝተዋል።
በወቅቱ ባንዳዎች ከጣሊያን ጋር ወግነው በሀገሪቱ ላይ ደባ ሲፈጽሙ የተመለከቱ የንጉሡ ተቀናቃኞች ጭምር ጥሪውን ተቀብለው በጋራ መታገላቸውንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያውያን በነበራቸው የአንድነት መንፈስ እና ሀገርን ከጠላት የመከላከል እልህ በጋሻ እየመከቱ፣ በጦር እና በጎራዴ በመፋለም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ወራሪ ኀይል ድባቅ በመምታት የሀገራቸውን ክብር ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ጭምር ቀና እንዲል አድርገዋል። ከዚህም ባለፈ ሠራዊቱ በአንድ ጠቅላይ አዛዥ መመራቱ፣ የአዛዦቹ የመረጃ አጠቃቀም እና ጠላትን የማሳሳት ዘዴ ከጠላት በልጦ መገኘት፣ ሠራዊቱ በጠላት ላይ የነበረው የመተባበር የቆየ ልምድ፣ የመሪዎቹ የማስተዳደር፣ የመምራት ብቃት እና ብልሃት ጋር ተዳምሮ ለድሉ በምክንያትነት ተቀምጠዋል።
ዚያድባሬ በ1969 ዓ.ም ያደረገውን ወረራ ለመቀልበስ የተደረገው ተጋድሎም ከቅርብ ጊዜ ታሪኮች ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት የሶማሊያ መሪ የነበረው ዚያድባሬ ታላቋን ሶማሊያ ለመገንባት ከነበረው ቅዠት በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ በ1969 ዓ.ም ወረራ ፈጽሟል፤ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ መንግሥት ወረራውን ለመመከት የእናት ሀገር ጥሪ አድርጎም ነበር፤ ጥሪውን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጣ እስከ 300 ሺህ የሚጠጋ ሕዝባዊ ሠራዊት በማሰለፍ ሀገሪቱን መታደግ ተችሏል፡፡ በዚህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለይ ከዳር እስከ ዳር የተነቃነቀው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሀገር ለማፍረስ የመጣውን የዚያድባሬ ወራሪ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ሀገሪቱን ከውርደት መታደግ ተችሏል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አዳነ እንዳብራሩት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል የፈጸመውን ወረራ ለመመከት ሁሉም ከጫፍ ጫፍ ተነስቶ እየተፋለመው ነው፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያዊነት ማስተሳሰሪያ ገመድ ሆኗል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በጋለ ስሜት ጦርነቱን ሕዝባዊ በማድረግ ሽብርተኛውን ኀይል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ ለህልውና ዘመቻው የሚደረገው ሕዝባዊ ማዕበል የተቀናጀና ግለቱን የጠበቀ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
መንግሥት ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት እና ሕዝባዊ አንድነትን መገንባት ከቻለ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መመከት የማይቻልበት ምክንያት እንደማይኖርም አስረድተዋል፡፡
ተጨማሪ የመረጃ ምንጭ፡- “ሰው” ከጲላጦስ (ኃይለጊዮርጊስ ማሞ) መጽሐፍ
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ