
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2012 ዓ/ም (አብመድ) የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን በጎንደር ከተማ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቅቀዋል።
ዘጠኝ አባላት ያሉት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የሚዲያ ልዑካን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ኪሮል ተወካይና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በሆኑት በቆሞስ እስጢፋኖስ የተመራ ነው።
በጎንደር ከተማ በነበራቸው ቆይታ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስትን፣ የደብረ ብርሃን ሥላሴን እና የሐዋሪያው ጳውሎስ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
በጎንደር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኅብረት ሰብሳቢ አቶ ብርሀኑ አያሌው በተለይ ለአብመድ እንደተናገሩት ጉብኝቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የጀመረችው መልካም ግንኙነት አካል ነው። ከኅብረቱ ጋር በልዩ ልዩ የማኅበራዊ ጉዳይ ልማቶች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ሀሳቦችን አንስተው ስለመወያዬታቸውም ገልፀዋል። የልማት ትብብር መስኮችም ከቤተ ክርስቲያኗ ባሻገር በጤና፣ በትምህርትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ጉዳይ መምሪያ የሚዲያ ዳይሬክተር መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በሰጡት መረጃ ደግሞ የጉብኝቱ አንድ አካል በሆነው የሐዋሪያው ጳውሎስ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አፍሪካንም የሚያገለግል የቲዎሎጂ ትምህርት ቤት የመክፈት ምክረ ሀሳብ መኖሩን ተናግረዋል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት በጎንደር ከተማ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
ዘጋቢ፦ ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ