ባንዳዎችን ከኢትዮጵያ ታሪክ የመሰረዝ ወቅቱ አሁን ነው!

351
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ልዩነት ቢኖር እንኳን ልዩነቶቻቸውን በይደር አቆይተው በጋራ ሲቆሙ አይደለም ኢትዮጵያን አፍሪካንም ከባርነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት ቀንዲል ሆነው አገልግለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጦርነት ብርቋ፣ ፈተና አዲሷ አይደለም፡፡ ወደቀች ስትባል ተነስታለች፤ ተበተነች ሲሏት ሌሎችን ሳይቀር ሰብስባለች፡፡ “ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሁልጊዜም ሲደማ ይኖራል” እንዲሉ አበው የባንዳ ልጆች ያስወጓት፣ ጎረቤቶቿ የወጓት እና የሩቅ ሀገራት ጠላቶቿ የከዷት ኢትዮጵያ በየክፍለ ዘመኑ ተፈትናለች፡፡ ዛሬም ከእናት ጡት ነካሾች የተሰነዘረባት ክህደት ካለፉት ፈተናዎቿ ያነሰ እንጂ የበለጠ አይደልም፡፡
ኢትዮጵያ እነዛን የፈተና ዘመን ወቅቶች በድል ስትሻገር እልፍ ሕይዎት ተገብሮ፣ አጥንት ተከስክሶ እና ደም ፈሶ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው በላይ የሚያስበልጧት ሀገር አለቻቸው ሲባል ተረት ሳይሆን እውነት ነው፡፡ “በጥቅምት እኩሌታ ወረ ኢሉ ከትተህ ጠብቀኝ” ተብሎ አዋጅ ከንጉሡ የታወጀለት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደሚወዳት በተግባር የሚያሳይበት እድል ስለገጠመው ፈጣሪውን እያመሰገነ ስንቅ እና ትጥቁን ይዞ ወረኢሉ ከትቷል፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝብ “ክተት” መባል እድል “ዝመት” መባል መመረጥ እና “አዋጅ” መስማት ብስራት ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘምቶ መሰዋት ጀግንነት፤ ፈርቶ መሸሽ ደግሞ ሞት የሚሆንበት ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡
በሀገሩ ድርድር የማያውቀው የአማራ ሕዝብም እየሞተ እንኳን ለሚስቱ ኩራትና ለሀገሩ መብራት ነው፡፡ እንደ ሻማ ቀልጦ ለነፃነት ፋና ወጊ የሆነው ሕዝብ ልጆቹ አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለው እንዲናገሩ በነዲድ ውስጥ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአያሌው ጀግኖች እና ለእናት ሀገራቸው ሲሉ መሰዋትን የሚመርጡ ቢሆኑም በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን ውስጥም የወየበ ቀለም ያጠላባቸው ባንዳዎችም ነበሩ፡፡
ለጣሊያን እንቁላል እየሸጠ ወገኑን ያስወጋ ኢትዮጵያዊ ትናንት የመኖሩን ያክል “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይ ግብዝ በዚህ ዘመንም ሀገር ለማፍረስ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ ከእነዚህ ግብዞች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ሽብርተኛው ትህነግ እና ደጋፊዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ምናልባትም በዓለም የሥነ መንግሥት ታሪክ የሚጠላትን ሀገር ያስተዳደረ ብቸኛው የማፈያ ቡድን ነው፡፡ በመንበረ ንግሥናው በህቡዕ የሚጠላትን ኢትዮጵያ ከመንበሩ በወረደ ማግስት ጥላቻውን በግልጽ አውጥቶታል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ከሥልጣኑ ከተባረረ ማግስትም የኢትዮጵያውያንና የአማራ ሕዝብ ነቀርሳ ሆኖ መቀጠሉ ነው፡፡ ልክ የዛሬ አንድ ዓመት የዓለም ታሪክ ሊመዘግበው የሚገባ እና ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲጠብቀው የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት በሚያሳፍር መልኩ ከጀርባው ወግቶ እብሪቱን ለዓለም ሕዝብ በገሀድ አሳየ፣ በኢትዮጵያዊያን ላይም የለመደ ክደቱን በተግባር አሳየ፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ክፉኛ የተመታው ሽብርተኛው ትህነግ በስምንት ወራት የዋሻ ውስጥ ቆይታው የክህደት ባህሪውን እንደገና ተላብሶ ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ ተመለሰ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በእብሪተኛው ቡድን በተከፈተው በዚህ ጦርነት ገሀድ የወጣ አንድ ሃቅ ቢኖር ሽብርተኛው ትህነግ ጦርነቱን ከቡድን ወደ ሕዝብ መቀየሩ ነው፡፡
አምኖበትም ይሆን ተገድዶ የትግራይ ሕዝብ በሽብር ቡድኑ እየተመራ የአማራ እና አፋር ክልሎችን በሚያሳፍር መልኩ ወርሯል፡፡ በወረራውም የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት በዘር ጭፍጨፋ፣ በዘረፋ፣ በውድመት እና አስነዋሪ ድርጊቶችን መፈጸም ሥራየ ብለው ተያይዘውታል፡፡
ከእናቶች መቀነት ፈትተው ያገኙትን ብር ወስደዋል፤ ጌጣ ጌጦችን ከአንገት እና ጆሮ እየነጠቁ ቀምተዋል፤ እንዲሁም የግለሰቦችን ቤት እና ንብረት መዝብረዋል፡፡ ይህ ሽብርተኛው ትህነግ ለሕዝብ ያለውን የበረታ ጥላቻ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ አሁን ኢትዮጵያውያን ሁለት ምርጫዎች ከፊታቸው ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው የማይጨው ጦርነት የክህደት ርዝራዦችን በተለመደው ኢትዮጵያዊ ወግ ዳግም ወረራ እንዳያስቡ አድርጎ መቅበር፡፡ ሌላኛው ደግሞ ያለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ግፍና በደል እንዲቀጥል መፍቀድ፡፡
የሽብር ቡድኑ ለወረራ ሲነሳ “በአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ፣ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” ማለቱ አይዘነጋም፡፡ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የተፈጠሩ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ሃይማኖታዊ ቀውሶችን ማሰብ ደግሞ ቢሳካለት ወራሪው ቡድን አማራ የሚባል ሕዝብ በምድር ላይ እንዳይኖር ለማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ የአማራ ሕዝብ የዘመናት ሕልውናው ተከብሮ እና ታፍሮ የኖረው በሌላ ሳይሆን በራሱ ኀይል ነው፡፡ ዛሬም የአማራ ሕዝብ ነፃነት በዘመኑ የአማራ ልጆች ተጋድሎ ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ የዘመናት ዝምታ እና ቸልተኝነት ጉዳዩን የቤተ ዘመድ ከማድረግ የመነጭ እንጂ የሚጠሉትን ፊት አይቶ የሚለይ፣ የራሱን የማይሰጥ እና ከሌሎችም የማይመኝ ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ አማራ ከወገኖቹ ጋር በመሆን ዘመቻውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል አጠናቆ እረፍት እና ሰላም የሚያገኝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ነፃነትና ክብርን በችሮታ ማግኘት አይቻልም!” የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው
Next articleየአማራ ክልል መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ የተቀበሉ የጎንደር ፋኖና ሚሊሻ አባላት ሽኝት ተደረገላቸው።