
ደባርቅ፡ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት ኑርሁሴን ሁሴን በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ከዛሪማ ከተማ ነው ተፈናቅሎ ደባርቅ የተጠለለው። ከአሁን በፊትም ቢኾን ለወገን ኃይል የሚኾን ስንቅ፣ ጥይትና ሌሎች ቁሳቁስን በማቀበል የኋላ ደጀን ኾኖ ሲያገለግል እንደቆየ ተናግሯል። የወገን ኃይል የወገንን ድጋፍ ስለሚሻ በተለይ ወጣቱ ሊደግፈውም ኾነ ጠላትን ሊታገል እንደሚገባ መልእክቱን አስተላልፏል። አሁንም ቢኾን ከጓደኞቹ ጋር በመኾን ለመዝመት ዝግጁ መኾኑን ነው ወጣቱ የተናገረው።
አቶ አብዱሸኩር አዲሴ የተባሉት ተፈናቃይ በሽብር ቡድኑ ምክንያት ተፈናቅሎ ከመሰቃየት ጠላትን ደምስሶ መስዋእት መኾን ይሻላል ብለዋል። ለመዝመት ዝግጁ እንደኾኑ የተናገሩት አቶ አብድሸኩር መንግሥት ወደ ግንባር እንዲያዘምታቸውም ጠይቀዋል።
ከዛሪማ ከተማ የተፈናቅሉት አቶ እንድሪስ ሐሰን ደግሞ “ከተማችንን ለጠላት ማስረከብ ስለሌለብን ሁላችንም ለመዝመት ዝግጁ ነን” ብለዋል። የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል አደረጃጀት ፈጥረው ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ታጀበ አስፋው የተባሉት ተፈናቃይ ጠላት በአካባቢያቸው ላይ ከፍተኛ ውድመት መፈጸሙን ተናግረዋል። ጠላትን ለመደምሰስ ወጣቱ፣ ሴቱ፣ ሽማግሌውና ቀሳውስቱ ለመዝመት ዝግጁ ኾነዋል ብለዋል።
ሦስት ልጆቻቸውን ለዘመቻው እንደላኩ የተናገሩት አቶ ታጀበ እሳቸውም ቢኾኑ ለመዝመት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ