
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የከፈተውን መጠነ ሰፊ ወረራ ለመቀልበስ የክልሉ መንግሥት የክተት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ የሽብር ቡድኑ ወረራውን ሕዝባዊ በማድረግ ሰብዓዊ ጉዳቶችን፣ ዘረፋና ውድመት እያደረሰ ነው ያለው የክልሉ መንግሥት ሕዝባዊ ወረራ የሚቀለበሰው በሕዝባዊ ማዕበል መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የገጠመንን የሕልውና ፈተና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የግልና የመንግሥት ታጣቂዎች፣ ሚሊሻ እና የሰለጠኑ የተጠባባቂ ኀይል አባላት ምዝገባ እየተካሄደ ነው ያሉት ተቀዳሚ ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ ምዝገባው ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት እና የልዩ ኃይል ምልመላ ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የገለጹት፡፡
የክተት ጥሪውን ተከትሎ የሚሰማራው ኀይል ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ከክልሉ እስኪወጣ ድረስ በጀግንነት ተልዕኮውን ይወጣል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህም ሲባል ግዳጁን የሚመሩ እና የሚያስተባብሩ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኅላፊዎች ከፊት ኾነው ይመራሉ ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ወደ ግንባር ለመሄድ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝባዊ ሠራዊት ተመዝግቧልም ተብሏል፡፡
መዝመት የሚችል የከተማዋ ወጣት ኹሉ ይህንን ታሪካዊ የክተት ጥሪ ተቀብሎ መዝመት ይኖርበታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ መዝመት የማይችለው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ የሎጀስቲክ እና የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃ ላይ በመሰማራት ሊያገለግል ይገባል ብለዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ (ዶ.ር) ክልሉ የሚገኘው በሕልውና ዘመቻ ውስጥ በመሆኑ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያስገባ ገደቦችን እና ግዳጆችን ሊያስቀምጥ ስለሚችል ሕዝቡ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ