
ደብረታቦር፡ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከአያቶቻችን የወረስነው ስለ ሀገር ፍቅር ራስን አሳልፎ መስጠት እና ስለ ሕዝብ ክብር መራራ መስዋእትነትን መጎንጨትን ነው። አማራ ሕልውናውን፣ ሀገሩን እና ክብሩን ለባንዳ አሳልፎ ከሚሰጥ ሞትን ይመርጣል።
አሁን የአማራነት ጥግ የሚፈተንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ነን። ይህ ወቅት አቅሙ የፈቀደ ሁሉ ከሽብርተኛዉ ትህነግ ወራሪ ቡድን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ዘመን ተሻጋሪ ታሪኩን በወርቅ ብዕር የሚከትብበት ፈታኝ የትግል ምዕራፍ ነው። በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ አማራ ማንነቱን የማስከበር፣ ታሪኩን የማደስ እና ሀገርን የመታደግ ታሪካዊ ኀላፊነት ተጥሎበታል።
በሰሜን ወሎ በኩል አድርጎ በደቡብ ጎንደር ወረራ የፈጸመው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ሕዝባዊ ሠራዊቱ እያደረሰበት ባለው ከፍተኛ ምት በገባበት ፍጥነት ጥሎ እየፈረጠጠ ነው።
የፖለቲካ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ የየአካባቢው ነዋሪዎች ለፀጥታ ኀይሉ ድጋፍ በማድረግ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይ ወጣቶች ሕዝቡን አስተባብሮ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን፣ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ እና ግንባር በመሰለፍ ጠላትን እየተፋለሙ ነው ፤ የንግዱ ማኅበረሰብም ሰፊ የግብዓት አቅርቦት በማድረግ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን ሕልም እንዲመክን የድርሻቸውን በመወጣት መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና የሚሊሻ አባላት አሸባሪውን ድባቅ እንዲመቱ ተጨማሪ ኀይል ሆነዋል።
ጠላት ከደቡብ ጎንደር ዞን ተጠራርጎ ከወጣ በኋላም ሕዝቡ ግንባር ተሰልፎ በመፋለም፣ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ጠንካራ ደጀንነቱን አስቀጥሏል።
ጠላት ወደ ዞኑ ለመግባት ካሰበበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ የነበረው ቁጣ እና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ውጤታማ ነበር ይላሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ይርጋ ሲሳይ።
የአማራ ክልል መንግሥት የክተት ጥሪ ካቀረበ በኋላ ትናንት ምሽት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ሁሉም ነገር ወደ ግንባር ሲል አውጇል።
የዞኑ አስተዳደር እና ሕዝቡ ጥሪውን ተቀብለው የመንግሥት ሠራተኛውን፣ ነጋዴውን ማኅበረሰብ፣ የታጠቀም ይሁን ያልታጠቀውን የኅብረተሰብ ክፍል አቅሙ እና እድሜው የሚፈቅድለትን በፍጥነት የማደራጀት ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው።
እየተደራጀ ያለው ኀይል ቀጥታ ወደ ግንባር በመዝመትም በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ወገን ነጻ ለማውጣት ከሠራዊቱ ጋር ይቀላቀላል። ለዚህም በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ኅብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን የማወያየት እና ለቀጣይ ስምሪት የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የወጣቱ ስሜት ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት የተወረሩ አካባቢዎችን ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድንን እስከወዲያኛው ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆናቸውን እና ግንባር ለተሰለፈው የፀጥታ ኀይል ተጨማሪ ጉልበት በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ዞኑ እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በወረራ ከፍተኛ ችግር ስለደረሰበት ሕዝቡ የጠላትን አስከፊነት ብቻም ሳይሆን የተወረሩ አካባቢዎችን እንዴት ነጻ ማድረግ እንደሚችልና የጠላትን አቅም ተረድቷል ነው ያሉት።
በከፍተኛ ወኔ፣ እልህ እና ተነሳሽነት ወደ ግንባር ለመሄድ የመጨረሻውን የድል ጽዋ ሊጎነጩ መነሳታቸውን ወጣቶች ተናግረዋል። እኛም መስዋእትነት ከፍለን ነጻነታችንን እናረጋግጣለን ነው ያሉት ወጣቶቹ።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ