
ደባርቅ፡ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት አሸባሪውና ወራሪው የትህነግን ቡድን እስከ መጨረሻው ለማጥፋት እንዲቻል ለትግል አቅሙ ብቁ የኾነ ዜጋ ኹሉ እንዲነሳ መጠየቁን ተከትሎ ጥሪውን በደስታ ከተቀበሉት ውስጥ የስሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ጀግኖች ይጠቀሳሉ።
አሚኮ ያነጋገራቸው የደባርቅ ወረዳ ጀግኖች እንዳሉት የክልሉ መንግሥት በሚያሰማራቸው ግንባሮች ኹሉ ጠላትን ለመደምሰስ ዝግጁ ናቸው።
አቶ ምስጋናው ክብረት ጠላት አካባቢያቸውን ለመውረር በመጣበት ወቅት ዳግም ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ ላይ እስኪደርስ መቅጣታቸውን ተናግረዋል። “የክልሉን መንግሥት ጥሪ የተቀበልነው እኛ ብቻ ሳንኾን ሴቱ፣ ወንዱ፣ አባቶች፣ እናቶች፣ ቄሱም መነኩሴውም ነው፤የሕዝብን ሃይማኖትና ማንነት የማያከብረውን አረመኔ ቡድን ያለበት ድረስ ሄደን ለመቅጣት ተሰልፈናል” ብለዋል።
ጥንትም ቢኾን “ስሜን ምን አለ?” ተብሎ እንደሚነገርለት ኹሉ ጠላት እስኪንበረከክ ድረስ እንቀጠዋለን ነው ያሉት።
አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት ዳር ድንበር እንደማይለዩ ነው አቶ ምስጋናው ያስገነዘቡት።
በከፍተኛ ቁጭትና ወኔ ስሜታቸውን የገለጹት አቶ ምስጋናው በወረዳቸው በርካታ ስመጥር የኾኑ ጀግኖች መሰለፋቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ፈረደ ታከለ የወረዳው ሕዝብ አሸባሪው ቡድን ለማጥፋት ቆርጦ መነሳቱን ተናግረዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይ የአማራ ሕዝብ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ መዝመት እንዳለበትም ተናግረዋል።

“አባቶቻችን በክብር ያስረከቡንን ሀገር እኛ አናዋርዳትም” ነው ያሉት። “ትግል ሴትና ወንድ ስለማይል ሊወረን የመጣን ጠላት ለማጥፋት ተዘጋጅቼያለሁ” ያለችው ደግሞ በዳባት ወረዳ ጠላትን በመቀጥቀጥ ዲሽቃ ማርከው ስማቸውን ከፍ ያደረጉት ወይዘሮ አስቴር ደመላሽ ናቸው። አሁንም መንግሥት ወደሚያሰማራቸው ግንባር ለመዝመት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ጠላት ሁሉንም ሰው በማሰለፍ እኛን እንዲወር እየላከ እኛ እንዴት ቤት እንቀመጥ?” ያሉት ወይዘሮ አስቴር መላው የአማራ ሕዝብ ማእበል በመፍጠር ጠላትን ሊያጠፋው እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ሴቶች ኹሉ ይነሱ፣ ይትመሙ፣ ደጀን በመኾን ይታገሉ” ብለዋል። ሀገር ከሌለ ኑሮ እንደሌለ የተረዱት ወይዘሮዋ ሁለት ልጆቻቸውንና የንግድ ሥራቸውን ትተው ለመዝመት መቁረጣቸውን ተናግረዋል።
13 የቤተሰብ አባላትን ትተው ከልጃቸው ጋር ለመዝመት የቆረጡት ደግሞ አቶ ዘመኑ ብዙነህ ናቸው። ወራሪውን ቡድን ለመቅበር መነሳታቸውን በከፍተኛ ቁጭት ነው ለአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን የተናገሩት። ልጃቸውም ከአባቱና ከቀሪ ጀግኖች ጋር በመኾን ጠንካራ ክንዱን በጠላት ላይ ለማሳረፍ መዘጋጀቱን ነው የተናገረው።

የደባርቅ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሰሎሞን ወርቁ ለትግል ብቁ የኾነውን ኹሉ ወደ ግንባር እያንቀሳቀስን ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ በነቂስ ኾኖ የክልሉን መንግሥት ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር እየተመመና የቀረውም ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ነው የብራሩት። በተለያየ ምክንያት በዘመቻው የማይሳተፉ የወረዳው የማኅበረሰብ ክፍሎች የዘማቾችን ሰብል እያሰባሰቡና ሌሎች ማኅበራዊ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ ሰሎሞን ጠቁመዋል።
የሽብር ቡድኑ ቆርጦ የተነሳው አማራና አፋርን በማጥፋት ኢትዮጵያን ማፍረስ ስለኾነ መላው ኢትዮጵያዊ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ- ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ