
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በጠቅላይ ሚኒስትር እና በፌዴራል እና በክልል አመራሮች በባሕርዳር በተካሄደዉ ዉይይት አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት የተለያዩ ዉሳኔዎች ተላልፈዋል ብለዋል። በዚህም መሰረት የአማራ ክልል የክተት ጥሪን ያስተላለፈ ሲሆን ሌሎች ክልሎችም የተለያዩ ዉሳኔዎችን እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በትላንትናዉ ምሽት ከ100 በላይ የኮምቦልቻ ወጣቶችን መግደሉንም አስታውቀዋል።
በደዋ ጨፋ አካባቢ የሚገኙ የኦነግ ሸኔ አባላትም አሸባሪውን ትህነግ በመደገፍ በቀቢጸ ተስፋ መንገድ ለመዝጋት ቢሞክሩም በአካባቢዉ ወጣቶች እና ሚሊሻ ድርጊቱ መክሸፉን አንስተዋል። ይህንን የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡ መንግስትም እርምጃ መዉሰድ ጀምሯል ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች ወደ ሽምቅ ዉጊያ የገቡ የማህበረሰብ ክፍሎችም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይህንን የሽብር ቡድን ለማጥፋት የክተት ጥሪዉን መቀላቀል ይገባል ብለዋል።
የመከላከያን ሥነ ልቦና ለመጉዳት በማኅበራዊ የትስስር መረቦች ላይ የተለያዩ መረጃዎችን በሚለቁ አካላት ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩንም አመላክተዋል።
አሸባሪው ቡድኑ አሁንም በደሴና በኮምቦልቻ የመንግስት እና የግል ንብረቶችን እያወደመና እየወሰደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ