
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶክተር) በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የተነሳውን የትህነግ የሽብር ቡድንን ለማጥፋት ሁሉም በየአካባቢው እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።
በቀጣይ ትግሉን ለማቀጣጠል አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ታታሪ ወታደር እና ታታሪ ሠራተኛ እንጂ ታታሪ ወረኛ አይደለም ብለዋል። ሀገሪቱ አሁን የተደቀነባትን የሕልውና አደጋ ለመመከት ከመደበኛ መከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኀይል በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለትግል እራሱን እንዲያደራጅ ነው ያሳሰቡት።
የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመመከት የወሎ ወጣቶች እንዳደረጉት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።
ኅብረተሰቡ ቀየውን ትቶ ከመሸሽ፣ ሰርጎ ገቦችን መከላከል እንዳለበት የተናገሩት ሚኒስትሩ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ የሚደረግ እንቅስቃሴም ሰርጎ ገቡን እና አስተኳሹን ለመለየት አስሸጋሪ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ አሸባሪው ቡድን በሄደበት ሁሉ እንዲቀበር ወጣቱ በርትቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው የገለጹት፡፡
ለእርዳታ ወደ ትግራይ የገቡ 860 ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ወራሪው እና አሸባሪው ትህነግ እርዳታ ታግዶባችኋል በሚል ማደናገሪያ ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና ሽማግሌዎችን በመንጋ ወደ ጦርነት እያሰለፈ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ሚኒስትሩ የአማራ እና የአፋር ክልልን በመውረር ዜጎችን ስቃይ ውስጥ የከተተውን ቡድን ለማጥፋት እና በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ በየትኛም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለማዳን እንዲነሳ ሀገራዊ ጥሪ መቅረቡን ነው የተናገሩት።
የሽብር ቡድኑ ጦረነቱን እያካሄደ ያለው በኢኮኖሚም ጭምር በመሆኑ አርሶ አደሩ ሰብሉን በመሰብሰብ ለቀጣይ የመስኖ ሥራ ይዘጋጅም ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ እንዲህ ሲሆን ኢትዮጵያን መታደግ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡-አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ